የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ሁሉም የአሜሪካ የጦር ኃይል አባላት በ2021 መጀመሪያ ወር ላይ ሶማሊያን ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጡ።
በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የእስላማዊ ፅንፍ እንቅስቃሴዎችን የመግታት ተልዕኮ ተሰጥቶት ሶማሊያ የሚገኘው 700 ያህል የአሜሪካ ሠራዊት እንዲወጣ የታዘዘው ተመራጭ-ፕሬዚደት ጆ ባይደን ቃለ መሃላ ከመፈጸማቸው አምስት ቀናት ቀደም ብሎ ጃኑዋሪ 15 ነው።
ይህም በሶማሊያ ይሰጥ የነበረውን ስልጠናና ይካሄድ የነበረውን ፀረ-ሽብር ተልዕኮ ፋይዳ አስመልክቶ ባልበረደው ክርክር ላይ ግለትን ጨምሯል።
በሶማሊያ የአሜሪካ ጦር ተልዕኮ ደጋፊዎችና የተወሰኑ ብርቱ የትራም ደጋፊዎች ዘንድ የሠራዊቱ መኖር አል ሻባብ በሪጂኑ ኃይሉን አጠናክሮ እንዳይስፋፋ የገታ መሆኑንና የጦሩ ሶማሊያን ለቅቆ መውጣትም ለሶማሊያ የጸጥታ ኃይላት የሚሰጡትን ስልጠናዎች የሚያቋርጥ መሆኑ ጉዳት እንዳለው በማንሳት ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ሆኖም የዩናይትድ ስቴትስ መከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣናት ዓርብ ዕለት እንዳስታወቁት ገሚሱ ጦር ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ በመዛወር እዚያ ሆኖ የድሮን አየር ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችል ጠቅሰዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ሶማሊያን ለቅቆ የሚወጣው አገሪቱ የፓርላማ ምርጫ ለማድረግ ስድስት ወራትና ፕሬዚደንታዊ ምርጫም ፌብሪዋሪ 2021 ለማከናወን በዝግጅት ላይ ባለችበትና የኢትዮጵያ ጦርም በአገር ውስጥ ወታደራዊ ግዳጆች ተጠምዶ ባለበት ወቅት ነው።
ፕሬዚደንት ትራምፕ ቀደም ብለውም በአፍጋኒስታንና ኢራቅ ካለው የአሜሪካ ጦር ከፊሉ እንዲመለስ ማዘዛቸው ይታወሳል።

