ቪክቶሪያ ከመሪ ኋላ ሆነው የሞባይል ስልክ የሚጠቀሙ አሽከርካሪዎችን ተቆጣጥረው የሚቀርጹ ካሜራዎቿን ከዛሬ ጁላይ 29 ጀምሮ የመጀመሪያ የሙከራ ተግባራቸው ላይ አሰማርታለች።
የቴክኖሎጂ ሙከራ ጊዜው የሚቆየው ለሶስት ወራት ሲሆን ከዚያ በኋላ በቋሚነት የቁጥጥር ሥራ ላይ ይውላል።
ኩዊንስላንድም በበኩሏ ከዚህ ሳምንት ጀምራ እስከዚህ ዓመት መጨረሻ የሚቆይ የሞባይል ስልክ የካሜራ ቁጥጥር ሙከራዋን ትጀምራለች።
የኩዊንስላንድ ሙከራ ሞባይል ስልኮችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የመኪናቸውን ቀበቶ ያልታጠቁትንም ያካትታል።
ሁለቱ ክፍላተ አገራት በሙከራ ጊዜያቶች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አውቶሞቢሎችን እያሽከረክሩ ሞባይል ስልኮቻቸውን ሲጠቀሙ በካሜራ ለተደረሰባቸው ሰዎች የመቀጮ ሳይሆን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው ያደርጋሉ።

የቴክኖሎጂ ሙከራው ተጠናቅቆ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ በሚውልበት ሰዓት ቪክቶሪያ ውስጥ እያሽከረከሩ ሞባይል ሲጠቀሙ የተገኙ ሾፌሮች $496 ዶላርስና አራት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ፤ ኩዊንስላንድ ውስጥ $1000 ዶላርስና አራት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ ያገኛቸዋል።
አውስትራሊያ ውስጥ የሞባይል ስልኮች ተቆጣጣሪ ካሜራ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ቀዳሚ ኒው ሳውዝ ዌይልስ ስትሆን፤ ቴክኖሎጂውን በሥራ ላይ ካዋለች አምስት ወራት ተቆጥረዋል።

በተቀሩት የአውስትራሊያ ክፍለ አገራት አዲሱ የሞባይል ስልኮች ተቆጣጣሪ ካሜራ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ባይውልም ሾፌሮች አውቶሞቢል እያሽከረከሩ ሞባይል ስልክ ሲጠቀሙ ከተገኙ መቀጮ ያገኛቸዋል።
የአውስትራሊያ ካፒታል ቴሪቶሪ፤ ሞባይል ስልክን በእጅ ይዞ መኪናን ማሽከርከር $480 ዶላርስና ሶስት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ - መኪና እየነዱ በሞባይል መልዕከት መለዋወጥ፣ ማኅበራዊ ግንኙነትን ማካሄድ፣ የሞባይል አፕ ወይም ኢንተርኔትን መጠቀም $589 ዶላርስና አራት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ ያስጥላል።
ደቡብ አውስትራሊያ፤ $534 ዶላርስና ሶስት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ
ምዕራብ አውስትራሊያ፤ $1000 ዶላርስና አራት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ
ኖርዘርን ቴሪቶሪ፤ $500 ዶላርስና ሶስት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮ
ታዝማኒያ፤ $336 ዶላርስና ሶስት የአሽከርካሪነት ነጥብ ቅነሳ መቀጮን ያስከትላል።

