ቪክቶሪያ 77 አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አስመዘገበች - ፖሊስ 300,000 ሰዎችን እየቃኘ ነው

ከ 300,000 በላይ ቪክቶሪያውያን ለሁለተኛ ጊዜ ገደቦች ተጥሎባቸዋል፤ ሌሎች ስቴቶችም አትምጡብን እያሉ ነው።

COVID-19 restrictions in Regional Victoria will be eased from midnight on September 16 with some of the restrictions eased in Melbourne

Source: AAP

ቪክቶሪያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 77 አዲስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።

ከ300,000 በላይ የሚኖሩባቸው ቀበሌዎቿ ላይም ገደቦችን ጥላለች። 

የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ ፕሮፌሰር ብሬት ሳተን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተስፋፍቶባቸው ካሉ ቀበሌዎች አልፎ ወደ ሌሎች እንዳይዛመት ለመቆጣጠር እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ቪክቶሪያ ውስጥ 415 ከቫይረሱ ያላገገሙ ሰዎች አሉ።   

ፕሮፌሰር ሳተን - መላ የቪክቶሪያ ነዋሪዎች አንዳቸው ካንዳቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ቁጥብ እንዲያደርጉ ሲያሳስቡ፤

"የቤት ውስጥ ቆይታ መመሪያዎች የሚመለከቱት ገደብ የተጣለባቸውን የፖስታኮዶች ቢሆንም፤ የእኔን ቤተሰብ አባላትና ጓደኞች ጨምሮ ሁላችንም በመላ ቪክቶሪያ ያለን ሰዎች አሁን ባለው ሁኔታ በእርግጥ ሌሎች ቤተሰቦችን መጎብኘት ያስፈልገን እንደሁ በውል ማሰብ ያሻናል" ብለዋል።  

ሜልበርን ባሉ 10 የፖስታኮዶች ወይም 36 ቀበሌዎች ላይ የቤት ውስጥ ቆይታ ገደቦች የተጣሉት ከዛሬ ሐሙስ ጀምሮ እስከ ጁላይ 29 ነው።  

ገደቦቹ የተጣሉባቸው ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ከቤታቸው መውጣት የሚችሉት ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለምግብና አስፈላጊ ነገሮች ሸመታ፣ ለአካል እንቅስቃሴ፣ ድጋፍ ለሚሹ ክብካቤ ለማድረግ ወይም ለራሳቸው ክብካቤን ማግኝት የሚሹ ሲሆን ብቻ ነው።

ገደቦቹ በሥራ ላይ መዋላቸውንም ለመቆጣጠር ፖሊስ ወደ ቀበሌዎቹ የሚገቡና የሚወጡት ላይ ቁጥጥሮችን ያካሂዳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ፕሮፌሰር ሳተን ቫይረሱ በተማሪዎች መካከል መተላለፉን ሲገልጡ፤

"በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተማሪ ወደ ተማሪና ከአስተማሪ ወደ አስተማሪ ተጋቦቶች ተከስተዋል" ብለዋል።

ትምህርት ቤቶቹ እንዲዘጉ መደረጉንም አክለው ተናግረዋል። 

በሌላም በኩል ለወሸባ ግልጋሎት የተመደቡ ሆቴሎች የድንጋጌ ጥሰቶችን መፈጸማቸው ተነግሯል።

 ኩባንያዎቹ ግልጋሎት ያልሰጡባቸውን ሰዓታት የሰሩ አስመስለው የግብር ከፋዮችን ገንዘብ እንደጠየቁና ጥቂት ጠባቂዎችን ብቻ በመመደብም ለወረርሽኙ ከፍተኛ ተጋላጭነት ሰበብ እንደሆኑ ሔራልድ ሰን ዘግቧል።

በተጨማሪም፤ የተወሰኑ ጠባቂዎች ከእንግዶች ጋር አብረው መተኛታቸው፣ እጅ ለእጅ መጨባበጣቸው፣ አሳንሱሮችን መጋራታቸውና የባሕር ማዶ ተመላሽ መንገደኞች ከአንዱ መኝታ ክፍል ወደ ሌላው እንዲዘዋወሩ የተፈቀደላቸው መሆኑም ተነግሯል።

አንድ ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ ጠባቂ ለ Nine Network እንደገለጸው ወደ ጥበቃ ሥራ ከመሰማራቱ በፊት የተሰጠው ስልጠና ለአምስት ደቂቃ ብቻ ነበር።

ይህ በእንዲህ አንዳለም፤ ኒው ሳውዝ ዌይልስ ከ10ሩ ገደብ የተጣለባቸው ፖስትኰዶች ወሰኗን ተሻግረው ከዘለቁ $11,000 የገንዘብ መቀጮ ወይም ለስድስት ወራት እሥራት እንደሚዳረጉ አስጠንቅቃለች።

ኩዊንስላንድ በሬ ለሁሉም ቪክቶሪያውያን ዝግ ነው፤ ለተቀሩት ስቴትና ግዛቶች ግና ከጁላይ 10 ጀምሮ ወሰኔ ክፍት ነው ብላለች። 

ደቡብ አውስትራሊያ ለቪክቶሪያውያን በቅርቡ ወሰኗን የመክፈቱን ዕሳቤ መደርደሪያ ላይ አኑራ፤ ከኒው ሳውዝ ዌይልስና የአውስትራሊያ መዲና ግዛት ጋር የጉዞ ስምምነት ለማድረግ አዝምማለች።

 


2 min read

Published

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now