ኮሮናቫይረስ የተስፋፋባቸው ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ ከነገ ረቡዕ እኩለ ለሊት ጀምሮ ከቤታቸው መውጣት የሚፈቀድላቸው ለአራት ምክንያቶች ብቻ ይሆናል።
- ለአካላዊ እንቅስቃሴ
- ወደ ትምህርት ቤት ወይም ወደ ሥራ ለመሔድ
- ድጋፍ ለሚሹ የክብካቤ ግልጋሎቶችን ለማበርከት
- ምግብና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለመሸመት
ቪክቶሪያ በዛሬው ዕለት ማክሰኞ 64 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።
በጠቅላላው ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,159 ደርሷል።
ይህንኑ አስመልክተውም አቶ አንድሩስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር "ተቀባይነት በሌለው መልኩ ከፍተኛ" ነው "ይህም ለሁላችንም ዕውን የሆነ ስጋት ደቅኗል" ብለዋል።
የቤት ውስጥ ቆይታ ገደቦቹ 10 የፖስታኮዶችን ይመለከታል
ፕሪሚየር አንድሩስ የቤት ውስጥ ቆይታ ገደቦቹ 10 የፖስታኮዶችን እንደሚመለከት ገልጠው፤ የቀዬዎቹ ነዋሪዎችም አዲሶችን ትዕዛዞች መፈጸማቸውን ለማረጋገጥ የፖሊስ ሠራዊት አባላት በአካባቢዎቹ እንደሚሰማሩ አስታውቀዋል።
ገደቦቹ የተጣሉባቸው የፖስታኮዶች፤ 3012, 3021, 3032, 3038, 3042, 3046, 3047, 3055, 3060 እና 3064 ናቸው።
ፕሪሚየሩ በማከልም - የቪክቶሪያ ነዋሪዎችን ሲያሳስቡ "በሚቀጥሉት አራት ሳምንታት ውስጥ በግል ልትከውኑት ግድ ለሚል ሥራ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ወደ እነዚህ የፖስታኮዶች እንዳትሄዱ" ብለዋል።
ቪክቶሪያ አውሮፕላኖች እንዳያርፉባት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠየቀች
አቶ አንድሩስ ዛሬ ማክሰኞ ዓለም አቀፍ በረራዎች ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ወደ ሜልበርን እንዳይዘልቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንን ጠይቀዋል። ይህንንም ጥያቄ ያቀረቡት ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የውጭ አገር ተመላሽ መንገደኞችን ወሸባ የማስገባቱና የመቆጣጠሩን ጫና እንዲቀንስ በማሰብ ነው።
ፕሪሚየሩ "ከሌሎች የስቴት መሪዎች ጋር በመነጋገር ሁኔታዎችን አስረዳለሁ፤ ጫናችንን ስለሚጋሩንም በቅድሚያ ምስጋናዬን አቀርባለሁ" በማለት ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ በቅርቡ ቁጥሩ ለናረው የቫይረሱ መስፋፋት አንዱ ሰበብ የወሸባ የአፈጻጸም ተግባሮችን የጣሱ የሆቴል ሠራተኞች መሆናቸው አመላክተዋል።
በሌላም በኩል፤ የፌዴራል ምክትል የሕክምና ኃላፊ ማይክል ኪድ በፕሪሚየር አንድሩስ የተጣሉ የቤት ውስጥ ቆይታ ገደቦችን አስመልክተው ሲናገሩ፤
"በቪክቶሪያ ፕሪሚየር የተወሰዱት እርምጃዎች ሕይወቶችን አዳኝ ናቸው" በማለት ድጋፋቸው ሰጥተዋል።

