የቀድሞው ምክትል ፕሪሚየር ቤን ካሮል ዛሬ ማክሰኞ ጁላይ 28 / ሐምሌ 21 አዲሱ የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ሆነው በሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባላት ተመረጡ።
አቶ ካሮል ለፕሪሚየርነት የበቁት የቀድሞዋ ፕሪሚየር ጃሲንታ አለን ተቀናቃኝ ሆነው በመቅረብ ወ/ሮ አለንን ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ጫና በማሳደርና የፓርቲያቸውን አብላጫ ድጋፍ በማግኘት ነው።
ፕሪሚየሯ ዛሬ ማለዳ ላይ የሌበር ፓርቲ የፓርላማ አባላት ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለፉክክር ከመቅረብ ይልቅ ከስብሰባው መጀመሪያ 30 ደቂቃ ቀደም ብለው ከስልጣን በፈቃዳቸው መልቀቃቸውን በማስታወቃቸው ፓርቲውን ለአራት ሳምንታት ከሚፈጅ የምርጫ ሂደት ታድገዋል።
ወ/ሮ አለን ለአዲሱ ተመራጭ ፕሪሚየር ቤን ካሮል ሙሉ ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልበኒዚ የወ/ሮ ጃሲንታን ስንብት አስመልክተው "ጃሲንታ መልካም ሰው ናቸው። ይህቺ ዕለት ለእሳቸው በእጅጉ አዋኪ ትሆናለች" ያሉ ሲሆን፤ አክለውም መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።
ከአዲሱ የፕሪሚየር ምርጫ ጋር ተያይዞም በቤን ካሮል ተይዞ የነበረውን የምክትል ፕሪሚየር ኃላፊነት ለመያዝ የወ/ሮ አለን ደጋፊ ሶንያ ኪልኬኒ ውጥን የነበራቸው ቢሆንም በእግራቸው ሲቲቭ ዲሞፖዩሎስ ተተክተው 23 ድምፅ አግኝተዋል።
ሆኖም ሌላዋ ዕጩ ጋብርየሊ ዊልያምስ 45 ድምፅ በማግኘት የምክትል ፕሪሚየር ኃላፊነቱን በአብላጫ ድጋፍ ተረካቢ ሆነዋል።
ሁለቱ አዲስ ተመራጭ የቪክቶርያ መንግሥት መሪዎች ቤን ካሮልና ጋብሪየሊ ዊሊያምስ እንደ ቅደም ተከተላቸው ፕሪሚየርና ምክትል ፕሪሚየር ሆነው ዛሬውኑ ቃለ መሐላ ፈፅመዋል።

