ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ቪክቶሪያ ላይ ተጥሎ የነበረው የኮረናቫይረስ ገደብ ከዛሬ ረቡዕ ዕኩለ ለሊት ጀምሮ እንደሚያበቃ አስታወቁ።
አቶ አንድሩስ ባለፉት 24 ሰዓታት 40,000 የኮሮናቫይረስ ምርመራዎች ውስጥ አንድም በቫይረሱ የተጠቃ ግለሰብ ውጤት አለመኖሩንም ገልጠዋል።
አያይዘውም፤ ምንም እንኳ ገደቦቹ ቢነሱም የተወሰኑ ገደቦች እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት፤
• ከቤት ለመውጣት የሚያበቁ የነበሩ አራት ምክንያቶች፤ ለአስፈላጊ ሸመታ ወደ ገበያ መሔድ፣ ከቤት ሆኖ ማከናወን ወደ ማያስችሉ ሥራ ወይም ትምህርት ቤት መሔድ፣ ክብካቤ ለማድረግና አካላዊ እንቅስቃሴ ብቻ ለማድረግ የነበሩት ተነስተዋል
• በአምስት ኪሎ ሜትሮች ብቻ ተወስኖ የነበረው የእንቅስቃሴ ገደብ ቀርቷል
• የችርቻሮና መስተንግዶ ግልጋሎት ሰጪዎች የአካላዊ ርቀት እንደተጠበቀ ሆኖ በሮቻቸውን ለደንበኞቻቸው ከፍተው ግልጋሎቶቻቸውን መስጠት ይችላሉ
• የሕዝብም ሆነ የግል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በ50 ፐርሰንት መጠን ወደ ሥራ ገበታቸው መመለስ ይችላሉ
• በቤተ እምነቶች አካላዊ ርቀት እንደተጠበቀ ሆኖ መሰባሰብና ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶችን ማካሄድ ይቻላል
• ለስፖርትና መዝናኛ ክንውኖች አካላዊ ርቀትን ጠብቆ መቀጠል ተፈቅዷል
• ሠርጎች አካላዊ ርቀትን ጠብቀው መካሔድ ይችላሉ
• የቀብር ሥነ ሥርዓቶች ያለ ለቀስተኞች ቁጥር ገደብ ይቀጥላሉ
• የመዝናኛና ሕዝባዊ ኩነቶች መቀጠል ይችላሉ
• ትምህርት ቤቶች ክፍት ይሆናሉ
የሚቀጥሉት ገደቦች እስከ ፌብሪዋሪ 27 ቀጣይ ይሆናሉ፤
• ማሕበራዊ ርቀትን ለመጠበቅ አዋኪ በሚሆኑባቸው በቤት ውስጥና ከቤት ውጪ ባሉ ሥፍራዎች ጭምብሎችን ማጥለቅ ግድ ይላል
• በቡድን የመሰባሰብ ብዛት መጠን ከ30 ሰዎች ወደ 20 ሰዎች ዝቅ ብሏል
• ቤት ውስጥ ለመሰባሰብ ቀደም ሲል ከነበረው 15 ጎብኚዎች ፈቃድ በአምስት ሰዎች ብቻ ተገድቧል

