አዘውትረው ስለ ዕፅዋቶች የሚናገሩትና 'በወይንና አይብ' የሚሽከረከር የስፖርት መኪና ያላቸው ቻርልስ ፊሊፕ አርተር ጆርጅ ማውንትባተን ዊንድዞር አውስትራሊያን አካትቶ የ14 የጋራ ብልፅግና አገራትና የአገረ እንግሊዝ ንጉሥ ሆነዋል።

ባርቤዶስ የፊታችን ኖቬምበር የእንግሊዝን ዘውዳዊው አገዛዝ ርዕሰ ብሔር ቁንጮነት ከሉዓላዊነቷ ላይ ከልታ ሪፐብሊክ ታቆማለች።
ለበርካታ ዓመታት በትዕግሥት የዘር ሐረጋቸው የፈቀደላቸውን የንግሥና ተራቸውን ሲጠብቁ የቆዩት ቻርልስ በ73 ዓመት አረጋዊ ዕድሜያቸው ለንግሥና በመብቃት በእንግሊዝ ወራሴ ዙፋን ባሕረ መዝገብ አዲስ ታሪክ አስቀልመዋል።
ምንም እንኳ በተወሰኑ ወገኖች ከተራው ዜጋ የራቀ አተያይ አለው ተብሎ የሚተቸው ዘውዳዊ አገዛዝ ተርታ ቢሰለፉም፤ ንጉሥ ቻርልስ ሳልሳዊ ለተፈጥሮ ጥበቃ ባላቸው ጥልቅ ድጋፍ፣ ችግረኛ ወጣቶችን በምግባረ ሰናይ ድርጅታቸው አማካይነት እርዳታ በመቸርና ፈትተው ያገቡ በመሆናቸው የዘመናዊውን ኅብረተሰብ ሕይወት "ይጋራሉ" ተብሎም ይነገርላቸዋል።
እ.አ.አ. ኖቬምበር 14, 1948 የተወለዱት ቻርልስ ቅድመ አያታቸው ያረፉትና በዙፋናቸውም እናታቸው ኤልሳቤጥ ለንግሥና የበቁት ገና የሶስት ዓመት ልጅ ሳሉ ነው።
ይሁንና በዕድሜ ገፍተው አካባቢያቸውን መገንዘብ ሲጀምሩ እሳቸውም አንድ ቀን ለንግሥና እንደሚበቁ ልብ ለማለት አፍታም አልወሰደባችውም።

ቤት ውስጥ በሚማሩት ዘውዳዊ ቤተሰብ ደረጃ ቻርልስ ወደ ትምህርት ቤትና ሲልም ዩኒቨርሲቲ ዘልቀው በመማር የመጀመሪያውና ዘመናይ የተሰኙ ናቸው።
ከትሪኒቲ ኮሌጅ፣ ካምብሪጅ ትምህርታቸውን በአንትሮፖሎጂ፣ አርኪዮሎጂና ታሪክ አጠናቅቀው የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ ለመሆን የበቁት በ1970 ነው።
ከዚያ፤ እምብዛም አልቆዩ ከሕይወት ፍቅረኛቸው ጋር ተገናኙ።
ፍቅርና ጋብቻ
የካሜላ ሻንድ ማኅበራዊ ሰንሰለት ከቻርልስ ጋር ተያያዥ የነበረ ነበርና ሁለቱ በዚያ ሁነት ተገናኙ። ወዲያውም ቻርልስ በ1971 በሮያል አየር ኃይልና ባሕር ኃይል ወታደራዊ ስልጠና ለመውሰድ ወደ ካምፕ ዘለቁ።
ወታደራዊ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ወደ ቤታቸው ሲመልሱ ግና ከካሚላ ጋር በይፋ ተለያዩ፤ ካሚላም በ1973 የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት መኮንን አንድሩ ፓርከር ባወልስን አገቡ።

ቻርልስ ከካሜላ ከተለያዩ በኋላ በርካታ የሴት ፍቅረኞች ነበሯቸው። ከቤት ውጭ እንቅስቃሴዎችም ፖሎ፣ ዓሣ ጠመዳ፣ የቀበሮ አደን፣ የበረዶ መንሸራተትን ያዘውትሩ ነበር።
እንዲሁም፤ ጠንካራ የአካባቢ ጥበቃ፣ ሥነ ጥበብና ሥነ ሕንፃ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አሳድረዋል፤ አስተዋፅዖም አበርክተዋል።

በ 1979 ቻርልስ ከዲያና ስፔንሰር ጋር ተዋወቁ።
ከሁለት ዓመታት በኋላም ለንደን ዌስት ሚኒስትር አቢ በባሕላዊ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ተጋቡ። ከ750 ሚሊየን በላይ የቴሌቪዥን ታዳሚዎችም የጋብቻውን ሥነ ሥር ዓት ባሉበት ሆነው ተከታትለዋል። በወቅቱ ቻርልስ 31 ዳያና 19 ዓመታቸው ነበር።

ልዕልት ዳያና ሁለት ወንዶች ልጆችን ዊሊያምና ሃሪን በ1982 እና 1984 ወለዱ። ይሁንና ጋብቻቸው በወቅቱ የታወከ ነበር። ቻርልስ ከቀድሞ ፍቅረኛቸው ካሚላ ጋር አብረው መኖር ይዙ ነበር። ዳያናም በወቅቱ ከጄምስ ሂዊት ጋር በትዳራቸው ላይ የጎንዮሽ ፍቅር እንደነበራቸው ተናግረዋል።
ብዙዎች የገመቱት አልቀረም በ1993 ልዑል ቻርልስና ልዕልት ዳያና ተለያዩ፤ በ1996 ጋብቻቸው ፈረሰ።
ከአራት ዓመት በኋላ ኦገስት 31,1997 ዳያና ፓሪስ ሳሉ በመኪና አደጋ ሕይወታቸው አለፈ።

ቻርልስና ካሚላ በ2005 ግርግር ባልበዛበት የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ተጋቡ። ቀጣዩን የንግሥና ሕይወታቸውንም አብረው ይቀጥላሉ።


