የአውስትራሊያዊቷን ድምፃዊትና ተዋናይት ኦሊቪያ ኒውተን-ጆን በ73 ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ተከትሎ "ውብ ነፍስ" እና "ታላቅ የመንፈስ አነቃቂ" የሚሉ የመታሰቢያ ውዳሴያዊ ቃላት በመላው አውስትራሊያ እየተደመጡ ነው።
በአገረ እንግሊዝ ተወልዳ፣ ብሪስበን አድጋ መኖሪያዋንን የካንሰር ምርምር ማዕከሏን ሜልበርን ላይ ያቆመችው ኦሊቪያ ደቡባዊ ካሊፎርኒያ በሚገኘው ቤቷ በቤተሰብ አባላት፣ ወዳጆቿና ባለቤቷ ጆን ኢስተርሊንግ ተከብባ በሰላማዊ ዕረፍት ለዘላለማዊ ስንብት መብቃቷ ተነግሯል።
ኦሊቪያ በ1978 ከጆንትራ ቮልታ ጋር ሆና የሳንዲ ኦልሰንን ገፀ ባሕርይ ተላብሳ በተወነችው "Grease" ከፍተኛ ዝናን አትርፋለች።

Australian singer and actress Olivia Newton-John and American actor John Travolta as they appear in the Paramount film 'Grease', 1978. Credit: Paramount Pictures/Fotos International/Getty Images
የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስም በበኩላቸው የሜልበርኑን የካንሰር ማዕከል በማንሳት ኦሊቪያ አስደማሚ አሻራዋን አኑራ ማለፏን አንስተዋል።
በርካታ የጥበብ ሙያ ወዳጆቿ፣ የካንሰር ማዕከል ሠራተኞችና ሕሙማን የሐዘን፣ አድናቆትና የምስጋና መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል።
***
የቀድሞው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የፍሎሪዳ መኖሪያ ቤታቸው በኤፍ ቢ አይ መፈተሹን አወገዙ።
ለቢሮው የፐሬዚደንቱን ቤት ፍተሻ አስባብ የሆነው አቶ ትራምፕ በርካታ ፕሬዚደንታዊ ሰነዶችን ወደ ፍሎሪዳ ቤታቸው ወስደዋል ከሚል ጥርጣሬ ጋር ተያይዞ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ ፌዴራል ሕግ መሠረት ያለ ሕጋዊ ፈቃድ ምስጢራዊ ሰነዶችን ዕውቅና ወዳልተሰጠው ሥፍራ መውሰድ ለአምስት ዓመታት እሥር ያበቃል።
አቶ ትራምፕ ፍተሻውን ለሚቀጥለው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውድድር እንዳይበቁ ለማሰናከል "የፍትሕ ሥርዓትን ለመሣሪያነት" የመጠቀም ድርጊት ነው ብለውታል።