ሩስያ ለሁለት ከዩክሬይን ተገንጣይ ክፍለ ግዛቶች ዕውቅናን ቸረች።
ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ከምሥራቅ ዩክሬይን ለተነጠሉት የዳህኔስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ እና የሉሃንስክ ሕዝብ ሪፐብሊክ ዕውቅና መስጠቷን በቴሌቪዥን አስታውቀው እንዳበቁ ጦራቸው የሁለቱ ሪፐብሊኮች "ሰላም አስጠባቂ" ኃይል ሆኖ እንዲቆይ አዝምተዋል።
ይህንኑ የአቶ ፑቲን እርምጃ አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጧል።
በተመድ የዩናይትድ ስቴትስ ቋሚ አምባሳደር ሊንዳ ግሪንፊልድ የሩሲያ ጦሯን በሰላም አስከባሪ ስም ወደ ምሥራቅ ዩክሬይን ማሰማራት "ለመላው ዩክሬይን፣ አውሮፓና ዓለም ብርቱ መዘዞችን ያስከትላል" ያሉ ሲሆን፤ አያይዘውም ይህ "ግልፅ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት ነው" ብለዋል።
የባይደን አስተዳደርም ፈጥኖ አዲስ የንግድና የፋይናንስ ማዕቀብ በሩስያ ላይ መጣሉን አስታውቋል።
በሌላም በኩል የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የሩስያ ተግባር "ተቀባይነት" የሌለው መሆኑን ጠቅሰው ሩስያ "ወደ ኋላዋ መመለስ" እንዳለባት አሳስበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከሩስያ በኩል እየተቃጣ ያለው የወረራ ስጋት እያየለ በመምጣቱ የአውስትራሊያ ዲፕሎማቶች ዩክሬይንን ለቅቀው እንዲወጡ ተወስኗል።
ከኪየቭ የለቀቁት ዲፕሎማቶች እርዳታ ለሚሹ አውስትራሊያውያን ፖላንድና ሮማንያ ሆነው የቆንስላ ግልጋሎቶቻቸውን እንደሚያከናውኑ ተነግሯል።

