አመሰራረቱ በ33ኛው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ሃሪ ትሩማን፤ ነፃ ለሆኑ የአፍሪካ ፣ እስያና ላቲን አሜሪካ አገራት የቴክኒክ እገዛ ለማድረግ የተነደፈውን “4 Point” ፕሮግራም ተከትሎ ፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ሽርካነትና USAID ከዋኝነት ነው።
የዘውዱ ሥርዓት ሲያከትም፤ በዘመነ ደርግ ኢትዮጵያ ፊትዋን ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ አዞረች። ሶሻሊስታዊ እጅ ለጤና ኮሌጁ ተዘረጋ። በምሥራቅ ጀርመኑ ካርል ማርክስ (አሁን Leipzig University) አማካይነት የሕክምና ፕሮግራም ታክሎበት፤ ከኅብረተሰብ ጤና ኮሌጅነት ወደ ጎንደር የሕክምናና የጤና ሳይንስ ኮሌጅነት ከፍ አለ።

Emperor Haile Selassie I (L), and President Harry S. Truman (R) Source: Courtesy of PD
ሲልም፤ በዘመነ ኢሕአዴግ ሌሎች ተጨማሪ ኮሌጆች (የማኅበረሰብ ጥናት፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ) ታክለውለት በአውሮጳውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2004 ወደ ዩኒቨርሲቲነት አደገ።
ዶ/ር ደሳለኝ መንገሻ፤ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ስለ ዩኒቨርሲቲያቸው ሲናገሩ በትናንት ታሪኩ በመኩራት፣ በእስካሁን ስኬቱ በመርካትና በመጪው ጊዜ ላይ ብሩህ ተስፋን በማሳደር ነው።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ ዘንድሮ ከትምህርት ማዕዱ የሚቋደሱ (የመደበኛ፣ የክረምትና ተከታታይ ተማሪዎችን አካትቶ) ከ47 ሺህ በላይ ተማሪዎች፤ 11 የዕውቀት ምንጭ የሆኑ ኮሌጆች፣ ከ84 በላይ የቅድመ ምረቃ ዲግሪ ፕሮግራሞችና ከ150 በላይ የድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች አሉት።

Source: Courtesy of PD

Dr Desalegn Mengesha Source: SBS Amharic
የኢትዮጵያ የትምህርት ጉዳይ ሲነሳ በእጅጉ አሳሳቢ ሆኖ ያለው የጥራት ነገር መነሳቱ አይቀሬ ነው። የአደባባይ ገመና ከሆነ አያሌ የመስከረም ወራት መጥተው ሔደዋል። ገናም በርካታ መስከረሞች ጠብተው ይሸኛሉ።
ዶ/ር ደሳለኝ የእሳቸውን ዩኒቨርሲቲ ጨምሮ በአገረ ኢትዮጵያ የሚታዩ የትምህርት ጥራት ጉድለት ምንጮች የሚሏቸውን ቀንጭበው ሲያነሱ፤
- ትምህርትን ማስፋት ላይ እንጂ ጥራት ላይ አለማተኮር፣
- በብቃትና በብዛት የሰለጠኑ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እጥረት (የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ መሆን)፣
- ደረጃውን የጠበቀ ምርምር የሚካሄድበት ላቦራቶሪ አለመኖር፣
- በተማሪውና በመምህሩ ዘንድ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችግር መኖር፣
- በአማርኛም በእንግሊዝኛ ቋንቋ መግባባት የማይችሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንዳሉ፣
- ኮምፒዩተር ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያዩ ተማሪዎች ማጋጠምና
- የሂሳብ፣ እንግሊዝኛና ፊዚክስ አስተማሪ ከሌለባቸው ትምህርት ቤቶች ተምረው የሚመጡ ተማሪዎችን ማግኘት በከፊል ከነቀሷቸው ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
ውጤቱም ትምህርትና ክህሎት እንዳይገናኙ የሚያደርግ መሆኑን ያመላክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥ አራት ነጥብ የሚያመጡ ብዙ ተማሪዎች ቢኖሩም፤ ግና ክህሎቱን ይዘዋል ብለው እንደማያምኑ ይገልጣሉ።
ጥራት፣ ጥራት፣ አሁንም ጥራት በሚል ድምጸት።
መፍትሔን ሲያመላክቱም፤ ከአጸደ ሕጻናት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ ከፍተኛ ሙዋዕለ ንዋይ መፍሰስ አለበት ባይ ናቸው። በተጨማሪም፤ ለወደፊቱ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ማስተማር እስከሚቻል ድረስ ተማሪዎችን ከልጅነታቸው ጀምሮ እንግሊዝኛ ቋንቋን አጥብቆ ማስተማር አንዱ መፍትሔ እንደሆነ በእጅጉ ያሳስባሉ።
በጤና ዘርፍም፤ አንድ አጠቃላይ ሆስፒታል (General Hospital) እንኳ በሌለባት የጎንደር ከተማ ብቸኛ የሆነው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የጎጃም፣ትግራይና የወሎ አካባቢ ታካሚዎችን ጨምሮ ለሰባት ሚሊየን ዜጎች የሕክምና አገልግሎትን ይሰጣል። ዕውነትነቱን ለመቀበል ኅሊናን የሚሞግት ቢሆንም።
ተግዳሮትና ስኬት ተቀናቃኝ ቢሆኑም፤ አካልና ጥላ ሆነው አይለያዩምና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገራዊ ዕውቅናዎችን ለማግኘት በቅቷል። በርካታ የልቀትና ስኬት ሽልማቶችን አግኝቷል። እ.ኢ.አ. በ2008 ከትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም በ2009 የላቀ የጥራት ውጤ በማስመዝገብ በኢትዮጵያ የጥራት ድርጅት ተመርጦ ከቀድሞው ፕሬዚደንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እጅ የክብር ሽልማትን አግኝቷል።
በአዋኪ ሁኔታዎች ውስጥ የመልካም ውጤት ድምሮችን አጉልተው ማየት ለሚሹት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ደሳለኝ፤ መጪው ጊዜ የተሻለ ማለፊያ ዘመንን ለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ይዞ ይመጣል የሚል ብሩህ ተስፋ አላቸው።

DR Desalegn Mengesha Source: SBS Amharic





