የጡረታ አበል ዋስትና የማጭበርበር ሙከራ
በአንድ የፓርላማ ስሚ150 ያህል አውስትራሊያውያን የጡረታ አበል ዋስትና ተቀማጫቸው ላይ የማስመሰል ስርቆት ተቃጥቶባቸው እንደነበረና ሆኖም አንድም የመንግሥት ሲስተም የማጭበርበር ድርጊት እንዳልተፈጸመበት ተገልጧል።
የማጭበርበር ሙከራው የተካሔደው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የፋይናንስ እገዛ የሚሹ አውስትራሊያውያን $10 000 በዚህ ዓመት፤ ተጨማሪ $10 000 በሚቀጥለው ዓመት ከጡረታ አበል ተቀማጫቸው ላይ እንዲያወጡ የተደረሰውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።
የአውስትራሊያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሪስ ከርሾው ለሕግ መወሰኛው ምክር ቤት ስሚ እንደገለጡት 150 የሚደርሱ ሰዎች ዝርዝር የግል መረጃዎችን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ለማጭበርበር ተግባር ለማዋልና ሲስተሙንም ለመሸርሸር ተሞክሮ እንደነበር ገልጠዋል።
የማጭበርበር ተግባሩ ጋር ንኪኪ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩት ላይ ምርመራ ለማካሔድ አምስት ማዘዣዎች እንደወጡና የማስመል ተግባሩ የተቃጣውም በቀጥታ የአውስትራሊያ ግብር ቢሮ በኩል ሳይሆን በተዘዋዋሪ በአንድ የታክስ ኤጀንት በኩል እንደሆነም ተጠቁሟል።
አውስትራሊያውያን የግል መረጃዎቻቸውንና የጡረታ አበል ተቀማጮቻቸውን ነቅተው እንዲጠብቁም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
ቫይረስ - ሲዳር ሥጋዎች
ብሩክሊን - ሜልበርን ካለው የዕርድ ሥጋ ማዘጋጃ ፋብሪካ ጋር ተያይዞ የተዛመተው ኮሮናቫይረስ 62 ሰዎችን አጥቅቷል።
በምዕራብ ሜልበርን የሚገኘው ሲዳር ሥጋዎች ፋብሪካ ውስጥ ሠራተኞቹ በቫይረሱ መጠቃታቸው የተገለጠው ባለፈው ወርኃ ኤፕሪል ሲሆን፤ ተዛማችነቱን ለመግታት በጤና ባለ ሥልጣናት እንዲዘጋ ተወስኗል።
አንድ በቫይረሱ የተያዘ የፋብሪካው ሠራተኛ በአቅራቢያው ፉይትስክሬይ ከሚገኝ ዱታ ጋህላ አረጋውያን መጦርያ ሠራተኛ ጋር ቅርርቦሽ በማድረጉ ቫይረሱ ወደ ጤና ሠራተኛ ተላልፏል።
ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ዛሬ ሐሙስ ረፋዱ ላይ በሰጡት መግለጫ ቪክቶሪያ ውስጥ ትናንት ማምሻውን ከተመዘገቡት አዲስ በቫይረሱ የተያዙ 14 ሰዎች ውስጥ 13ቱ ከእርድ ሥጋ ማዘጋጃ ፋብሪካው ጋር ንኪኪ ያላቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የፋብሪካው ሠራተኞች ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታዎቹ መጤዎች ናቸው።
ቫይረስ - የአዕምሮ ጤና
ኮሮናቫይረስ በሚያስከትላቸው የምጣኔ ኃብት ድቅቀት ሳቢያ በሚከሰቱ የእዕምሮ ጤና ተፅዕኖዎች አውስትራሊያ ውስጥ ራስን በራስ እጅ ማጥፋት እስከ 50 ፐርሰንት ሊንር እንደሚችል ከወዲሁ ተገምቷል።
የብሬይን እና ማይንድ ማዕከል ድርሞ (በአጭሩ የቀረበ) የጥናት ዘገባ እንዳመለከተው ራሳቸውን ከሚያጠፉት ውስጥ 30 ፐርሰንት ያህሉ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 25 የሚገኙት ይሆናሉ።
የማዕከሉ ዳይሬክተር ኢያን ሂኪ - የሥራ አጥነት የወጣቶች አዕምሮ ላይ ተፅዕኖ የማሳደሩ ክብደት እጅጉን የገዘፈ መሆኑን አመላክተዋል።
የፌዴራል መንግሥቱ የጤና ሚኒስትር ግሬግ ሃንት መንግሥት ለአዕምሮ ጤና ግልጋሎት ሰጪዎች ማጠናከሪያ የሚሆን ተጨማሪ $500 ሚሊየን መመደቡን አስታውቀዋል።
የአዕምሮ ጤና መረጃ ወይም ድጋፍ የሚሹ ከሆነ ወደ ላይፍላይን በ 13 11 14 ይደውሉ።

