"በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ እየተካሄደ ያለው ቤቶችን የማፍረስና በግዳጅ ማስነሳት እርምጃ መኖሪያ ቤት አልባነትን አባብሷል"ኢሰመኮ

“በማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች ይገባል” - ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

EHRC.jpg

Credit: EHRC

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትናንት መጋቢት 22 ቀን 2015 ቤቶችን የማፍረስና በግዳጅ ማስነሳትን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቅርቡ በአዲስ መልክ በተደራጀው የሸገር ከተማ አስተዳደር የቤቶች ፈረሳ እና በግዳጅ ማስነሳት (Demolition and Forced Eviction) እየተከናወነባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መነ አብቹ እና በዙሪያው ከሚገኙ አካባቢዎች ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው ሰዎች በግል እና በቡድን ለኮሚሽኑ ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ ከየካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ክትትልና ምርመራ ሲያደርግ መቆየቱን አመልክቷል።

አክሎም፤ ምንም እንኳ የክትትልና የምርመራ ሥራው ሙሉ በሙሉ ባይጠናቀቅም የደረሱትን ቅሬታዎች የመስክ ምልከታ ማድረጉን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ ያሰባሰባቸውን መረጃዎችና ማስረጃዎች ተመርኩዞ እየፈረሱ ያሉ ቤቶችን በአራት ዘርፎች ፈርጇል።

በዚህም መሠረት፤

የመጀመሪያው ክፍል፤ ከ2005 ዓ.ም. በፊት የተገነቡ ቤቶች ሲሆኑ እነዚህን ቤቶች በተመለከተ በሀገሪቱ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ በወጣው አዋጅ ቁጥር 721/2004 አንቀጽ 6(4) እና (5) እንደተደነገገው አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በኢመደበኛ መልኩ የተገነቡ ቤቶች የከተሞችን ፕላን እና የሽንሻኖ ስታንዳርድ ሲያሟሉ ወደ መደበኛ ሥሪት እንደሚዞሩ ደንግጓል።

ነገር ግን ኮሚሽኑ ባደረገው ማጣራት እነዚህን ቤቶች ሕጉ በደነገገው መሠረት በወቅቱ ወደ መደበኛ ሥሪት እንዲዘዋወሩ የሚያስችላቸውን መስፈርቶች ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የማዘዋወር ሥራ ሳይሠራ እንዲሁ እንዲፈርሱ መደረጋቸውን ለመረዳት ችሏል።

ሁለተኛው ክፍል፤ በግዢ የተገኙ ቤቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ቤቶች ውስጥ መደበኛ ካርታ፣ የአየር ላይ ካርታ እና አረንጓዴ ደብተር ያላቸው እንዲሁም እንዳይፈርሱ የፍርድ ቤት እግድ ያለባቸው ቤቶች ከከተማ ፕላን ጋር የማይሄዱ ናቸው ከተባለ፤ በሕግ አግባብ በተደነገገው መሠረት ተለዋጭ የቤት መሥሪያ ቦታ እና ተገቢው ካሳ ተከፍሏቸው መነሳት የሚገባቸው ነበሩ።

ቤቶቹ በገጠር መሬት ላይ የተሠሩ ናቸው የሚባል ቢሆን እንኳ በኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደር እና አጠቃቀም አዋጅ ቁጥር 130/1999 አንቀጽ 6(8) መሠረት በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ንብረቶቻቸውን እንዲያነሱ ይደረጋል እንጂ በድንገት ማፍረስ አይገባም ነበር።

ሶስተኛው እና አራተኛው ክፍል፤ ከአርሶ አደሮች ጋር በተደረገ ሕገ ወጥ የመሬት ሽያጭ በተገኘ ቦታ ላይ የተሠሩ ቤቶች እና ከ2005 ዓ.ም. በኋላ ያለሕጋዊ ፈቃድ በመንግሥት ይዞታዎች ላይ የተገነቡ ቤቶች መሆናቸውን ገልጧል።

አያይዞም፤ እርምጃው ያለ በቂ የቅድመ ማስጠንቀቂያ (ቀድሞ የማሳወቅ ግዴታ) የተከናወነ፣ አድሎአዊነትን የተላበሰ ስለመሆኑ፣ እሥር፣ የአካልና ሥነ-ልቦና ጉዳት እና እንግልት ማድረሱን አስገንዝቧል።

“ስለሆነም በዚህ የማፍረስና በግዳጅ ማንሳት እርምጃ ለተጎዱ ሰዎች በሕጋዊ መንገድ የመኖሪያ ቤት ሊያገኙ የሚችሉበት መንገድና ለደረሰባቸው የንብረት ውድመት ሊካሱ የሚችሉበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች ይገባል” ብሏል።

የኢሰመኮ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራ ክፍል ዳይሬክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረሚካኤል በበኩላቸው “ኢመደበኛ ይዞታዎቸን መከላከል የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም የማፍረስና በግዳጅ የማንሳት እርምጃዎች ሰዎች ሕይወታቸው እንዲናጋ እና ቤተሰብ እንዲበተን የሚያደርግ መሆን የለበትም፤ ይልቁንም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች የተከበሩበት አሠራር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

Share

Published

By Stringer Report
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service