ኒው ሳውዝ ዌይልስ በኮሮናቫይረስ ማገርሸት ሳቢያ በተወሰኑ ሥፍራዎች የፊት ጭምብል የማጥለቅ ግዴታን ጣለች።
በዚህም መሠረት፦
- የገበያ ማዕከላት
- ሲኒማዎች
- የእምነት ቤቶች
- የፀጉርና የቁንጅና ሳሎኖች
- የጌም መጫዎቻዎች
- የሕዝብ ትራንስፖርትና
- የመዝናኛ ሥፍራ ሠራተኞች
የፊት ጭምብል የማድረግ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፕሪሚየር ግላዲስ በርጂክሊያን ሲድኒ ትላልቅ ኩነቶችን ለማተናገድ ተሰናድታ ባለችበትና ሠራተኞችም ወደ መደበኛ የሥራ ገበታቸው በሚመለሱበት ወቅት የፊት ጭምብል የማድረግ ግዴታን የመጣሉ ወቅታዊነት ተገቢ ጊዜ ላይ መሆኑንና ከእኩለ ለሊት ጀምሮም ግብር ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ መንግሥት የፊት ጭምብል የማድረግ ድንጋጌን እንዲያሳልፍ ከጤና ባለ ሙያዎች ብርቱ ግፊት የደረሰበት ሲሆን ከአውስትራሊያ የሕክምና ባለ ሙያዎች ማኅበር በኩልም በፍጥነት ገደቦችን ባለመጣል ብርቱ ትችት ተሰንዝሮበታል።
ቪክቶሪያ
ቪክቶሪያ ባለፉት 24 ሰዓታት ሶሶት ሰዎች በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸውን አስመዘገበች።
ይህም በጠቅላላው ቪክቶሪያ ውስጥ በቫይረሱ የተጠቁትን ሰዎች ቁጥር 32 አድርሷል።
የቪክቶሪያ ኮቨድ-19 ምርመራ ፕሮግራም አዛዥ ጄሮን ዌይማር የቪክቶሪያ ነዋሪዎች ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሥፍራዎች ለማወቅ የቪክቶሪያ ጤና ድረ-ገጽን እንዲጎበኙ አመላክተዋል።