የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የኢትዮጵያ ጉዳዮች ተጠባቢ ቡድን በእጅጉ አሳሳቢ የሆኑ የኢትዮጵያን ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በገለልተኛ መርማሪዎች የሚካሔድ ምርመራን መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አሳሰበ።
የኮሚሽኑ ሰብሳቢ፤ መሐመድ ቻንዴ ኦትማን ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከሆነ በመፈፀም ላይ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፣ መጠነ ሰፊ አመፅና አለመረጋጋት ለመፃዒ አስከፊ የወንጀል ተግባራትና ከተጠያቂነት ማምለጥ አስባብ እንደሚሆኑ አመላክተው፤ ባለፈው ወር የኮሚሽናቸው ሪፖርት ውስጥም ኢትዮጵያ ውስጥ ከኖቬምበር 3 ቀን 2020 አንስቶ የጦር ወንጀሎችና ሰብዓዊ ወንጀሎች ስለ መፈፀማቸው ከድምዳሜ ላይ የደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሰሜን ኢትዮጵያ የኖቬምበር 2022 የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መካሔዳቸውም የተመለከተ ሲሆን፤ በብርቱ ወንጀልነት የሚጠቀሱ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች መካሔዳቸውም ተጠቅሷል።
በተያያዥነትም የኤርትራ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ መኖርና በተለይም የፆታ ጥቃቶች መፈፀም ያልተቋረጠ መሆኑን፤ እንዲሁም በአማራ ክልል ከሕግ / ፍርድ ቤት ብይን ውጪ የሚካሔዱ ግድያዎች፣ የጅምላ እሥራት መካሔድንና ተገቢ ምላሾች ነፈጋዎችን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየቀረቡ መሆኑን አመላክቷል።
የሐዘን ቀናት
በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሔደው ጦርነት ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ የሕወሓት ተዋጊዎችን ለቤተሰቦቻቸው ሥርዓተ ሐዘንን ጠብቆ ለማርዳትና ዝክረ መታሰቢያም ለማድረግ ከኦክቶበር 13 / ጥቅምት 2 አንስቶ ለሶስት ቀናት እንደሚካሔድ ተነግሯል።
በዝክረ መታሰቢያው የመጀመሪያ ዕለትም ሕይወታቸውን ያጡ ተዋጊ አባላት ስም ዝርዝር በይፋ እንደሚነገር የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔራል ታደሰ ወረደ አስታውቀዋል።