ማሞ ምህረቱ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆሊዲንግስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት አማካሪና የንግድ ጉዳዮች ተደራዳሪ የነበሩ ሲሆን፤ ቀደም ሲልም በዓለም ባንክ ውስጥ በከፍተኛ ባለሙያነት አገልግለዋል።
ከጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ነሐሴ 28 ቀን 2017 በብሔራዊ ባንክ ገዢነት ያገለገሉት ማሞ ምህረቱ በገዛ ፈቃዳቸው ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ይፋ ያደረጉት በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ነው።
አቶ ማሞ፤ በምስጋናና ስንብት መልዕክታቸው ለብሔራዊ ባንክ ገዢነት ይሁንታቸውን የቸሯቸውንና ለሥራቸውም ስኬት ድጋፋቸውን እንደለገሷቸው የጠቀሷቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን አመስግነዋል።
ባለፉት 50 ዓመታት ባልታየ መልኩ በእጅጉ ብርቱ የሆነ የሀገር በቀል ምጣኔ ሃብት ፕሮግራም ላይ ከቀረፃ እስከ ትገበራ የአመራር አሻራቸው ያለበት መሆኑን አንስተዋል።
ተሰናባቹ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ አክለውም በፋይናንስ መስክ የውጭ ባንክ አገልግሎቶችን፣ የዘመነ የዲጂታል ኣካታችን እንዲከፍት ማስቻላቸውን፣ ሲልም፤ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክን ከመሰሉ የውጭ የፋይናንስ ሽርካዎች 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ማስገኘታቸውን፣ በእሳቸው አመራር ወቅትም የዋጋ ግሽበት ዝቅ ማለቱንና የዲጂታል ክፍያ ከፍ ለማለት መብቃቱን በአንኳርነት ነቅሰው አመላክተዋል።
የአቶ ማሞን ስንብት ተከትሎም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ነሐሴ 28 ባወጣው መግለጫ፤
"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክቡር ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ በስራ ዘመናቸው ላበረከቱት ልዩ አመራርና ላሳዩት የአገልግሎት ቁርጠኝነት ልባዊ ምስጋናው ይገልፃል። ክቡር ገዢው በአገልግሎት ላይ በነበሩበት ወቅት ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለበርካታ ዓመታት ሲጠበቁ የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርሞችን ተግባራዊ አድርገዋል።
"የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ክቡር ገዢ አቶ ማሞ ምሕረቱ ላሳዩት ከፍተኛ የሆነ የአመራር ጥበብ እና ቁርጠኝነት የተሰማውን ጥልቅ ምስጋና እየገለጸ የወደፊት የስራ ዘመናቸው ስኬታማ እንዲሆን ልባዊ ምኞቱን ይገልጻል" ብሏል።
ተሰናባቹ የባንክ ገዢ በማን እንደሚተኩ እስካሁን በይፋ አልተነገረም።