"በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል" ኢሰመኮ

“መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” - የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ

The feed and the handcuffs of a prison security officer.jpg

The feed and the handcuffs of a prison security officer. Credit: MARVIN RECINOS/AFP via Getty Images

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግ ንቦት 28 ቀን 2015 ባወጣው መግለጫ "በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ አካባቢዎች እየጨመረ የመጣውን የአስገድዶ መሰወር (Enforced Disappearance) በአስቸኳይ እንዲቆ" ጥሪ አቅርቧል።

አክሎም፤ ተይዘው የሚገኙበት ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር ላይ የሚገኙ (Incommunicado Detention) ሰዎችን ጉዳይ ሲከታተል መቆየቱን አመላክቷል።

ኮሚሽኑ አሳሳቢ ድርጊቶቹ በተለይም ጎልተው የሚከሰቱባቸውን አካባቢዎች አዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሚያ ክልል እና የአማራ ክልል መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎች በማነጋገር፣ በልዩ ልዩ የተጠርጣሪዎች ማቆያ ቦታዎች በመዘዋወር እና ከቤተሰቦችና ከሌሎች የመረጃ ምንጮች መረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን አስታውቋል።

መግለጫው አክሎ በሰጠው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ ገና ያላጸደቀችው ቢሆንም ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) መሠረት አስገድዶ መሰወር ማለት ‘’በመንግሥት ወኪሎች ወይም ከመንግሥት ፈቃድ ወይም ድጋፍ በተሰጣቸው ሰዎች ወይም ቡድኖች ወይም በመንግሥት ስምምነት አንድን ሰው በማሰር፣ አፍኖ በመውሰድ፣ ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድ ነጻነቱን በማጥፋትና፤ በቁጥጥር ስር መዋሉን በመካድ፣ በመደበቅ፣ የአለበትን ቦታ ባለማሳወቅ ወይም ደብዛውን በማጥፋት ፈጽሞ ከሕግ ጥበቃ ውጪ እንዲሆን ማድረግ’’ መሆኑን አስረድቷል።

በሌላ በኩል አንድን ሰው የሚገኝበትን ቦታና ሁኔታ ሳይታወቅ በእስር መያዝ (Incommunicado Detention) ማለት በተለይ በከባድ ወንጀል ተጠርጥሯል የተባለን ሰው ለወንጀል ምርመራ በሚል ምክንያት ከቤተሰብ እና ከጠበቃ እንዳይገናኝ አድርጎ በእስር የማቆየትን ተግባር የሚገልጽ ፅንሰ ሐሳብ ሲሆን፤ እነዚህ ሁለቱም ድርጊቶች ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ናቸው።

 በተለይ በአስከፊነቱ የሚታወቀው የአስገድዶ መሰወር ተግባርን የሚያቋቁሙት ዋነኛ አላባዎች (Elements of the Crime) ሦስት ዋና ጉዳዮች ሲሆኑ፤ እነዚህም:-

(ሀ) በማናቸውም ዓይነት መንገድ ቢሆን አንድን ሰው ከፈቃዱ ውጪ ነጻነቱን መንፈግ/ማጥፋት፣

(ለ) መንግሥት በጉዳዩ ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ፈቃድ ወይም ድጋፍ ወይም ስምምነት በመስጠት ተሳታፊ መሆን፣ እና

(ሐ) አስገድዶ የተሰወረውን ሰው ያለበትን ቦታ እና ሁኔታ መካድ፣ አለመቀበል ወይም ለማሳወቅ ፈቃደኛ አለመሆን ናቸው ሲል አስረድቷል።

ኮሚሽኑ በርካታ የሆኑ በእገታ የመሰወር ክስተቶችን በናሙናነት የነቀሰ ሲሆን፤ እያደረገ ያለውን ምርመራ አከናውኖ ሲያበቃም ይፋ እንደሚያደርግ ከወዲሁ አመላክቷል።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው “ይህ አስከፊ የሆነ የአስገድዶ መሰወር ድርጊት በአስቸኳይ እንዲቆም መንግሥት አስፈላጊውን ጊዜያዊ እና ዘለቄታዊ እርምጃዎች ሁሉ እንዲወስድ፣ የተሰወሩ ሰዎች ሁሉ በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ፣ በተሰወሩበት ጊዜ ሁሉ የተፈጸሙ ድርጊቶች ላይ የተሟላ ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ችግሩ የደረሰበትን አሳሳቢ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ሀገር አቀፍ ገለልተኛ አጣሪ የሥራ ቡድን በማዋቀር የድርጊቱ ሰለባ የሆኑ ሰዎችን ማፈላለግ እና ፍትሕን ማረጋገጥ ይገባል” በማለት አሳስበዋል።

 ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “መንግሥት የአስገድዶ መሰወር ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ሰዎች መፍትሔ መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ወንጀል ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ይረዳ ዘንድ፤ ሁሉንም ሰዎች ከአስገድዶ መሰወር ለመጠበቅ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት (International Convention for the Protection of All Persons from Enforced Disappearance) ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ተቀብላ እንድታጸድቅ ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።










Share

Published

By Stringer Report
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
"በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣው ሰዎችን አስገድዶ የመሰወር ድርጊት በአስቸኳይ ሊቆም ይገባል" ኢሰመኮ | SBS Amharic