ኮሚሽኑ እንዳስታወቀው ነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 24, 2014 በታጣቂዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል፣ እንዲሁም ከ20ሺህ በላይ ሰዎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ ኦቦራ ከተማ ፈልሰዋል።
የኮሚሽኑ መግለጫ አክሎም፤ "በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ የኦሮሞ ነትጻነት ሠራዊት (በተለምዶ "ኦነግ ሸኔ" ተብሎ የሚጠራ) ታጣቂዎች የወረዳው ዋና ከተማ የሆነችውን ኦቦራ ከተማን ለመያዝ ባደረጉት እንቅስቃሴ ሦስት የአማራ ብሔር ተወላጆች መግደላቸውን ተከትሎ ከኡሙሩ ወረዳ፣ ህሮ አዲስ ዓለም ከተባለ ቀበሌና አጎራባች ከሚገኘው የአማራ ክልል፣ ቡሬ ወረዳ የተወጣጡ ታጣቂዎች በኡሙሩ ወረዳ በሚገኙና አገምሳ፣ ጆግ ምግር፣ ታም ኢላሙ፣ ጀቦ ዶባን፣ ጦምቤ ዳነጋበ፣ ጃውጅ፣ ኛሬ፣ ለገ ሚቻ፣ ሉቁማ ዋሌ በሚባሉ ቀበሌዎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ነዋሪዎች ላይ ነሐሴ 24 እና 25 ቀን 2014 ጥቃት ፈጽመዋል" ብሏል።
በሁለቱ ቀናት በተካሔዱት ጥቃቶች ሳቢያም ከ60 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ70 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የነዋሪ ቤቶችና የቀንድ ከብቶች መዘረፋቸውን ኮሚሽኑ ካነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተረዳ መሆኑንም ገልጧል።
በዞኑ ውስጥ ባሉ ሌሎች ወረዳዎችም ጥቃቶች መድረሳቸውንና የፀጥታና ደኅነት ስጋቶች ሰፍነው ያሉ መሆኑን የኮሚሽኑ መግለጫ አያይዞ ያመለከተ ሲሆን፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለም በበኩላቸው በደረሱት ጥቃቶች ማዘናቸውንና ሁነቱ ያሳሳባቸው መሆኑን ተናግረዋል።