ከጳጉሜ 3 እስከ ጳጉሜ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደው 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ ተከፍቷል።
“ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማሳለጥ፣ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፍሪካ እየገጠሟት የሚገኙ አንገብጋቢ ፈተናዎችን በዘላቂነት መሻገር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግበት ተገልጿል።
አፍሪካውያን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን የሚመክሩበትና የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት የሚደገፍበትን አማራጭ የሚያጤኑበት እንደሚሆንም ይጠበቃል።
ጉባኤው በዋናነት በሁለት አጀንዳዎች ላይ መሰረት አድርጎ እንደሚካሄድ የተገለጸ ሲሆን፤ በቅድሚያ የአፍሪካን የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት መሰረት ያደረጉ አህጉራዊ መፍትሄዎች ዕውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

The logo of the Second Africa Climate Summit (ACS2) is displayed at the entrance to the plenary hall during the opening of the High-Level Leaders Summit in Addis Ababa, on September 8, 2025. Credit: LUIS TATO/AFP via Getty Images
በጉባኤው ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን በጋራ መከላከል የተሻለ ውጤት ለማምጣት ያላትን አቋም እና ያከናወነቻቸውን ተግባራት በጉባኤው ታንፀባርቃለች ተብሎ ይጠበቃል።
በመድረኩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የአህጉር አቀፍ የራስ መተማመን፣ አንድነትና የንፁህ ኢነርጂ ምልክት ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህ ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ታዳሽ ሃይል እንደሚያመነጭ ጠቁመዋል።
እኛ እዚህ የመጣነው የዓለምን ቀጣይ የአየር ንብረት ኢኮኖሚ ለመንደፍ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አፍሪካ ስነ ምህዳሯን ሳታጠፋ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ፈጣን እድገት ያስመዘገበች የመጀመሪያዋ አህጉር ልትሆን እንደምትችል ተናግረዋል።
ማክሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 የተመረቀው የሕዳሴው ግድብ ከ 3 ሚሊዮን የሚልቁ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጭስ ከተሞሉ ኩሽናዎችና የእናቶችንና ሴቶች የእለት ተእለት ሸክሞችን እንደሚያቀል ገልጸዋል።

Prime Minister of Ethiopia Abiy Ahmed delivers his remarks during the official inauguration ceremony of the Grand Ethiopian Renaissance Dam (GERD) in Guba, on September 9, 2025. Ethiopia inaugurated the continent's largest hydroelectric project on Tuesday, with Prime Minister Abiy Ahmed calling it a "great achievement for all black people" despite years of diplomatic rancour over the dam with downstream neighbour Egypt. Credit: LUIS TATO/AFP via Getty Images
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፤ የአየር ንብረት ራዕይን እውን ለማድረግ በሁለት ግንቦች ላይ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ በዚህም አፍሪካ ወጥ የሆነ ተሳትፎዋን ማጠናከር እንዳለባት ተናግረዋል።
አፍሪካ በቂ ሀብትና ወጣት የሰው ሀይል ቢኖራትም ማደግ ባለባት ልክ ባለማደጓ የዓለም አቀፍ ስርዓቱ አህጉሪቱን ወደ ኋላ የሚጎትቱትን መዋቅራዊ መሰናክሎች ማፍረስ እንዳለበት ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የተባበረች የአፍሪካን ድምፅ እያቀረብን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የአየር ንብረትን ጨምሮ ስልታዊና የተቀናጁ መፍትሄዎችን ለመፍጠር እየሰራን ነው ብለዋል።
ለሶስት ቀናት በሚቀጥለው በዚህ ጉባዔ ንግግር ያደረጉትን የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ፣ የጂቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር መህሙድ አሊ ዩሱፍን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና ተወካዮች ተገኝተዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ ከአዲስ አበባ ]