ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ጳጉሜን 4/2017ዓም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከሌሎች ጥሪ ከተደረገላቸው የተለያዩ አገራት መሪዎች ጋር በይፋ መርቀዋል።
የአፍሪካ እና ካሪቢያን መሪዎች ተወካዮቻቸው በግድቡ ምረቃ ላይ ተገኝተው ምርቃቱን ተካፍለዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኦማር ጌሌ፣ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር፣ የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሐሙድ፣ የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የባርቤዶሷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ፣ የስዋቲኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚሶ ድላሚኒ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማሕሙድ ዓሊ ዩሱፍ እና የተመድ ምክትል ዋና ጸሐፊ እና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ክላቨር ጋቴቴ ተገኝተዋል።

የዛሬ 14 ዓመት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ሲሆን 5,150 ሜጋ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቅርቡ ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንደምትገነባ ገልጸዋል።
በንግግራቸውም፤
ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ጥቂት ጊዜያት ህዳሴን የሚስተካከል ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ የሚውል የኒውኪሊየር ተቋም ግንባታና በአፍሪካ ግዙፉ የአየር ማረፊያ ግንባታ ይጀመራል ብለዋል።
የመጀመሪያው የጋዝ ፋብሪካ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ይመረቃል፤ ከእሱ በ10 እጥፍ የሚበልጥ ሁለተኛው የጋዝ ፋብሪካ ግንባታ በምርቃቱ ቀን ይጀመራል።
የጋዝ ማውጣት ሂደቱ ከተጀመረ በወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ ሥራና በቅርቡ የተፈረመው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ይጀመራል።
በመጪዎቹ አምስትና ስድስት ዓመታት በትንሹ 1.5 ሚሊየን ቤቶች ይገነባሉ ሲሉ ተናግረዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ የተገኙት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሼክ መሀመድ "ኢትዮጵያ ያስመረቀችው የህዳሴ ግድብ በቀጠናው ላሉ ህዝቦች ሁሉ ታሪካዊ ቀን ነው፡፡ በቀጠናው የሚፈለገውን እድገትና ብልጽግና ለመፍጠር በጋራና በመተማመን መስራት ይገባል፡፡ለዚህም ሶማሊያ የጎረቤት ሀገራት ሰላምና እድገት ለሚያጠናክሩ ተግባራትን በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት" ብለዋል፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው "ዛሬ የዓባይ ግድብ ምርቃት ለጋራ ራዕያችን ወንድማዊ ትብብርን ማጠናከር እንዳለብን ያመላከተ ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን የፓን አፍሪካኒዛም መገለጫ ነው። መላው አፍሪካውያንም መሰል ትልቅ ፕሮጀክት መስራት እንደምንችል ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡

ሩቶ አክለውም አፍሪካውያንንም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚያስተሳሰር እና የታዳሽ ኃይል ተደራሽነትን የሚያስፋፋ ፕሮጀክት መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አፍሪካ ከፍተኛ የሆነ የኢነርጂ ፍላጎት እንዳላት ያነሱት ፕሬዚዳንቱ ፍላጎቱን ለማሟላት የኢነርጂ ኢንቨስትመንት ላይ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል፡፡ ኬንያ ከህዳሴ ግድብ ከሚመነጨው ኃይል ለመግዛት ስምምነት እንደምታደረግም ተናግረዋል፡፡
[ ደመቀ ከበደ ፡ ከአዲስ አበባ ]

