የግማሽ ዋጋ የአውሮፕላን ቲኬቶች የአውስትራሊያን ቱሪዝም ኢንዱስትሪ በሚደጉመው የ $1.2 ቢሊየን ዶላር በጀት ውስጥ የተካተተ ሲሆን፤ 800 ሺህ የድጎማ ቲኬቶችን መጠቀም የሚችሉትም ከኤፕሪል እስከ ጁላይ በድጎማ ዕቅዱ ወደ ተመረጡ 13 ሪጂኖች የሚጓጓዙ የአገር ውስጥ ቱሪስቶች ይሆናሉ።
የተመረጡት የቱሪስት መዳረሻ ሪጂኖችም፤ ጎልድ ኮስት፣ ሳንሻይን ኮስት፣ ኬይንስ፣ ዘ ዋይትሰንዴይስ፣ ኤሊስ ስፕሪንግስ፣ ሎንሴስተን፣ ብሩም፣ ሪጂናል ቪክቶሪያ፣ ሜሪምቡላና ካንጋሩ አይላንድ ናቸው።
ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የተመደበው የድጎማ ገንዘብ ከቲኬቶች ግማሽ ዋጋ ቅናሽ ባሻገር፤ አየር መንገዶቹ የዓለም አቀፍ በረራዎች እስኪጀምሩ ድረስ ሠራተኞቻቸውን በሥራ ላይ እንዲያቆዩ ማገዣም ጭምር ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የድጎማው ትኩረት ሥራዎችን ለመታደግ እንደሆነ ገልጠዋል።
የቨርጂን አውስትራሊያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጄይን ኸርዲሊካ በበኩላቸው ድጎማው ቨርጂን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኙ በፊት ከነበረው የበረራ አቅም ከ50 ወደ 70 ፐርሰንት ከፍ እንዲል የሚያደርገው መሆኑን ተናግረዋል።
የኳንታስ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለን ጆንስ በፊናቸው ክፍለ አገራት ወሰኖቻቸው ላይ ተጨማሪ ገደቦችን እንደማይጥሉ ያላቸውን ተስፋ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኛ የ ፍላይት ሴንተር ማኔጂንግ ዳይሬክተር ግራሃም ቱርነር የ 1.2 ቢሊየን ዶላሩ ድጎማ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚኖረው እገዛ እምብዛም እንዳልሆነ በመጥቀስ ዋናው ጉዳይ "የአገር ውስጥ ወሰኖችንና የዓለም አቀፍ ድንበሮችን በተቻለ ፍጥነት ክፍት ማድረግ መቻል ነው" ሲሉ አሳስበዋል።
የአውስትራሊያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ቡድናትም በበኩላቸው የድጎማው መጠን አነስተኛ በማለት የቅሬታ ድምፆቻቸውን አሰምተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ከነገ ዓርብ ማርች 12 ከጠዋቱ 10:00 am ጀምሮ ለመኝታ ግልጋሎቶችና ቱሪስት መስህቦች 400 ዶላር ላወጡ የቪክቶሪያ ቱሪስቶች የ200 ዶላር ተመላሽ የገንዘብ ቫውቸር በቪክቶሪያ መንግሥት በኩል ይሰጣል።
የቫውቸሩ ተጠቃሚ ለመሆን ካሹ በነገው ዕለት 10:00 am https://www.vic.gov.au/regional-travel-voucher-scheme ድረ ገጽን በመጎብኘት መመዝገብ ይችላሉ።
የቪክቶሪያ መንግሥት ቀደም ሲል ባካሄዳቸው የሁለት ዙሮች ቫውቸር ድጎማ ቪክቶሪያውያን $200 ዋጋ ያላቸው 110 ሺህ ቫውቸሮችን ተጠቅመዋል።
ከመጀመሪያው ዙር ቫውቸር ተጠቃሚዎች ብቻ የሪጂናል ቪክቶሪያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ የ85 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት በቅቷል።