በአዲስ አበባ በተለምዶ ኃይሌ ጋርመንት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው የአፍሪካ መንደር (African Village) የተገነባው የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ዋና መሥሪያ ቤት ተመረቀ።
ማዕከሉ ከቻይና መንግስት በተበረከተ 80 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ሲሆን፤ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሺን ጋንግ እና የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በተገኙበት ጥር 3 ቀን 2015 ተመርቆ ሥራ ጀምሯል።
በምረቃ ሥነ ስርዓቱ ላይም በአፍሪካ ሕብረት የቻይና አምባሳደር ቻንግቹን፣ በኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት አባል አገራት አምባሳደሮች እና በኢትዮጵያ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ተወካዮች ተገኝተዋል።
ማዕከሉ 90 ሺሕ ሜትር ስኩዌር አጠቃላይ ስፋት ላይ ያረፈ ሲሆን፤ የድንገተኛ አደጋ ኦፕሬሽን ማዕከል፣ የመረጃ ማዕከል፣ የላቦራቶሪ፣ የስልጠና ማዕከል፣ የኮንፈረንስ ማዕከል፣ ቢሮዎች እና አፓርታማዎችን እንዳሉት ተነግሯል።
ሹመት
በኳታርና የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር የነበሩት ምስጋኑ አረጋ ጥር 2 ቀን 2015 በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስትር ደኤታ ሆነው ተሹመዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ሚኒስትር ደኤታ ከመሾማቸው በፊት ከ2021አንስቶ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነ በመሥራት ላይ ነበሩ።