አቶ አልባኒዚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቀለበት ያሰሩ የመጀመሪያው የአውስትራሊያ መሪ ሆነዋል።
አያሌ የሌበር ፓርቲ ባለስልጣናት፣ የሥራ ባልደረቦችና ዜጎችም የ "እንኳን ደስ አላችሁ" መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
አልባኒዚና ሃይደን ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት በወርኅ ማርች 2020 ሜልበርን ውስጥ በተካሔደ አንድ የንግድ እራት ግብዣ ላይ ነው።
በእራት ምሽቱ ወቅት አቶ አልባኒዚ እሳቸው የሚደግፉት የደቡብ ሲድኒ የአውስትራሊያ እግር ኳስ ቡድን ራቢቶስ ደጋፊ እንዳለ ሲጠይቁ፤ ሃይደን "እኔ አለሁ" በማለት ምላሽ ሰጡ።
አጋጣሚዋ አስባብ ሆና መጠጥ እየተጎነጩ ሊያወጉ በመካከለኛው ምዕራብ ሲድኒ ኒውታውን ከሚገኘው የወጣት ሄንሪ ቢራ መጥመቂያ በቀጠሮ ተገናኙ።
ፍቅር ተጀመረ፤ ሰረፀ፤ ለሠርግ ለሚያደርሰው ቀለበት በቃ።
የ45 ዓመቷ ሃይደን ያደጉት በኒው ሳውዝ ዌይልስ ማዕከላዊ የባሕር ዳርቻ ሲሆን፤ በጡረታ አበል ኢንዱስትሪ ለረጅም ጊዜያት በሙያተኝነት ሠርተዋል።
ጋብቻ ሲፈፅሙም ለሃይደን የመጀመሪያ፤ ከቀድሞ ሚስታቸው ካርሜል ቲበት በ2019 ለተፋቱት አልባኒዚ ሁለተኛ ይሆናል።