የእሥራኤል ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ ለፋሲካ በዓል ሥነ ሥርዓት ወደ እሥራእኤል በቡድን የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች እንዳይገቡ መመሪያ መስጠቱን የእሥራኤል ብዙኅን መገናኛዎች አስታወቁ።
ኢትዮጵያውያን የክርስትና እምነት ተከታዮች በየዓመቱ የሚከበረውን የትንሣእኤ በዓል በቡድን ወደ እሥራኤል ተጉዘው ከዕለተ ስቅለት ዓርብ ጀምረው ኢየሩሳሌም ውስጥ ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲያከብሩ ቆይተዋል።
ሆኖም የእሥራእኤል ባለስልጣናት በበዓለ ትንሣኤ ስም ወደ እሥራኤል የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ላይመለሱ ይችላሉ በሚል ስጋት በዘንድሮው የቡድን መንፈሳዊ የትንሣኤ በዓል ተጓዦች ላይ እገዳ ጥለዋል።
ይህንኑ አስመልክቶም የሥነ ሕዝብና ኢሚግሬሽን ባለስልጣን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የእርስ በእርስ ጦርነቱ ጋር ተያይዞ "ቱሪስቶቹ ላይመለሱ" እንደሚችሉ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለእሥራኤል ቱሪዝም ኤጄንሲዎች መላኩን የሚዲያ አውታሮቹ ዘግበዋል።
ደብዳቤው እሥራኤልን ለመጎብኘት የሚሹ ኢትዮጵያውያን በግለሰብ ደረጃ የኢሚግሬሽን ባለስልጣንን በኦንላይን ማግኘት እንደሚችሉ ማስፈሩም ተገልጧል።
ዘገባዎቹን አስመልክቶ የኢሚግሬሽን ባለስልጣን በሰጠው ምላሽ "ላለፉት ዓመታት ወደ እሥራኤል በቡድን ከኢትዮጵያ የመጡ ቱሪስቶች ወደ አገራቸው አልተመለሱም፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ [እሥራእኤል ውስጥ] ቀርተዋል" ብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ እሥራኤል 3,000 ቤተ እሥራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለመውሰድ ከውሳኔ ላይ መድረሷ ተነግሯል።
እሥራኤል ቤተ እሥራኤላውያኑን ለመውሰድ ዘለግ ላለ ጊዜ ስታንገራግር እንደንበረና ከይሁንታ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ግድ የተሰኘችው ሩስያውያንና ቱክሬናውያን ስደተኞችን ለመቀበል ከመፍቀዷ ጋር ተያይዞ ከደረሰባት ብርቱ የአድሎኝነት ትችት ጫና ሳቢያ እንደሆነም ተመልክቷል።
እሥራኤል በይፋ የምትቀበላቸውን የሩስያውያንና ዩክሬናውያንን ስደተኞች ቁጥር ይፋ ባታደርግም ከ30,000 እስከ 50,000 ሳይደርሱ እንደማይቀሩ የጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት ቢሮ ምንጮች መጠቆማቸው ተዘግቧል።
ምርጫ ደቡብ አውስትራሊያ
ቅዳሜ ከሚካሔደው የደቡብ አውስትራሊያ የክፍለ አገር ምርጫ በፊት የፖስታ ድምፅ መስጫ ጠያቂዎችና የአካል ቅድመ ዕለተ ምርጫ ድምፅ ሰጪዎች ቁጥር በእጥፍ ጨመረ።
የደቡብ አውስትራሊያ የምርጫ ኮሚሽን እንዳስታወቀው ከ 135 ሺህ በላይ [[135,417]] መራጮች ከቅዳሜው ዋና የምርጫ ቀን በፊት ቀድመው ድምፃቸውን ሰጥተዋል። በቅድመ ምርጫ በአብዛኛው ተሳታፊ ሆነው የተገኙት በገጠር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ናቸው።
በፖስታ የምርጫ ድምፃቸውን ለመስጠት 162,467 መራጮች አመልክተዋል።
እንዲሁም፤ ተጨማሪ 4300 በኮቪድ-19 የተጠቁ ወይም የቅርብ ንኪኪ ኖሯቸው ራሳቸውን አግልለው ያሉ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ካሉበት ሥፍራ ወጥተው ለመወሰድ ጠይቀዋል።
የምርጫ ኮሚሽን ማይክ ሼሪ እንገለጡት ወሸባ ገብተው ያሉ መራጮች የድምፅ መስጫዎችን በአቅራቢያቸው ካሉ የኮቪድ ምርመራ መስጫ ወይም የፈጣን አንቲጄን መመርመሪያ ማደያ ሥፍራዎች ሔደው መውሰድ ይችላሉ።