ባለፉት 24 ሰዓታት ቪክቶሪያ በኮሮናቫይረስ የተጠቃ አንድ ሰው ብቻ ስታመዘግብ አንዳችም ሕይወት አላለፈም።
የሜልበርን የ14 ቀናት አማካይ የቫይረሱ ተዛማችነት ቁጥር ወደ 8.1 ሲወርድ የሪጂናል ቪክቶሪያ 0.5 ደርሷል።
ምንጫቸው ያልተለየ የቫይረስ ተዛማች ቁጥሮች ወደ 17 ከፍ ብለዋል።
የቪክቶሪያ ዋና የጤና ኃላፊ የዛሬ ቅዳሜ የቫይረሱ ተዛማች ቁጥር ወደ አንድ ማሽቆልቆል በጣሙን ደስ ያሰኛቸው መሆኑን ገልጠዋል።
በሰሜናዊ ቪክቶሪያ ሺፐርተን ባለፈው ሳምንት የሶስት ግለሰቦችን በቫይረሱ መያዝ ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ለኮቨድ - 19 ምርመራና በመቶዎች የሚቆጠሩትን ለወሸባ ቢዳርግም ባለፉት 24 ሰዓታት አንዳችም በቫይረሱ የተጠቃ ግለሰብ አልተመዘገበም።
የቫይረሱን ማሽቆልቆል ተከትሎ አያሌ ሜልበርናውያን ነገ ይፋ በሚሆነው የገደቦች መርገብ ላይ ለቀቅ ያለ መላላቶች እንዲደረጉ ቢሹም የፕሪሚየር አንድሩስ መንግሥት ምን ያህል ገደቦችን እንደሚያላላ ግልጽ አይደለም።
ከሰኞ ኦክቶበር 19 የኮቨድ - 19 ገደቦች መርገብ በኋላ በኦክቶበር 26 የቫይረሱን የመስፋፋት መጠን ውጤት ተመርኩዞ የደረጃ ሶስት ገደቦችን በተጨማሪ የማላላት እርምጃዎች ይወሰዳሉ።