ዓረባዊ ገፅታን ተጎናፅፎ፣ ሙስሊሙንና እስያን አካትቶ በማንፀባረቅ ኅዳር 11 በተካሔደ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ የተጀመረው የኳታር ፊፋ ዓለም ዋንጫ 2022 በመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ማምሻውን ሊጠናቀቅ ሰዓታትን እየቆጠረ ነው።
በተካሔዱት ውድድሮች 63ቱ የተጠናቀቁ ሲሆን፤ 64ኛውና የመጨረሻው የዋንጫ ግጥሚያ 'አሸናፊው ማን ይሆን?' በሚል የአያሌ እግር ኳስ አፍቃሪዎችን ስሜት ሰቅዞ ባለው የፈረንሳይና አርጀንቲና ፍልሚያ ይደመደማል።

ለፍፃሜ ግጥሚያ የሚወዳደሩት ፈረንሳይ በ1998 እና 2018 እንዲሁም አርጀንቲና በ1978 እና 1986 አሸናፊ በመሆን ለሁለት ጊዜያት ለዓለም ዋንጫ ባለቤትነት የበቁ ናቸው።

ጠቅላላ ወጪው ከ220 ቢሊየን ዶላር በላይ የፈጀው የዓለም ዋንጫ 2022 በ15 ደቂቃ ልዩ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይጠናቀቃል።
የውድድሩና የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ የሚካሔደው በኳታር ሉሴይል ስታዲየም ነው።

አሸናፊ ማን ሊሆን ይችላል?
ዮናስ ሙሉጌታ፤ በቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር በጅሮንድ - አርጀንቲና

ኢዮብ እሱባለው፤ የይድነቃቸው ተሰማ ማኅበራዊ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚደንት - አርጀንቲና

ሳምሶን ከበደ፤ በቪክቶሪያ የኢትዮጵያ ባሕልና ስፖርት ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት - ፈረንሳይ

የፍፃሜ ግጥሚያ ሠንጠረዥ
ፈረንሳይ እና አርጀንቲና (በአውስትራሊያ ሰዓት አቆጣጠር ሰኞ ዲሴምበር 19 / ታሕሳስ 9) 2:00 am [AEDT]
ስርጭቱን በቀጥታ እንደምን መመልከት ይችላሉ?
በ SBS TV እና SBS On Demand
ቀጣዩ 23ኛው የዓለም ዋንጫ 2026 የሚካሔደው የት ነው?
በሶስት የሰሜን አሜሪካ አገራት፤
ዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳና ሜክሲኮ በጥምር በሚያዘጋጁባቸው 18 ከተሞች።

