በኳታር ሉሴይል ስታዲየም እጅግ ልብ ሰቃይ የነበረው የፈረንሳይና አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ ግጥሚያ በሙልና ተጨማሪ ጊዜያት ግጥሚያ ያለ አሸናፊ 3 ለ 3 አቻ መለያየት ያመራው ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ነበር።
ግቦቹን ለአርጀንቲና ያስቆጠሩት ሊዮኔል ሜሲ በ23ኛውና 108ኛ ደቂቃ (በፍፁም ቅጣት ምት)፣ አንሄል ዲ ማርያ በ36ኛው ደቂቃ ሲሆኑ፤ በፈረንሳይ በኩል ካይሊያን ዕምባፔ በ80ኛ (በፍፁም ቅጣት ምት)፣ 81ኛ እና 118ኛዎቹ ደቂቃ (በፍፁም ቅጣት ምት) በተከታታይ ሶስት ግቦችን አስቆጥሯል።
አቻ መለያየታቸውን ተከትሎ ወደ ለአሸናፊ ቡድን መለያነት በተሰጠው የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት አርጀንቲና ፈረንሳይን 4 ለ 2 በሆነ ውጤት ረትቶ ለዋንጫ ባለቤትነት በቅቷል።
በ2002 ብራዚል ጀርመንን አሸንፎ የዓለም ዋንጫ ባለቤት ከሆነ ከ20 ዓመታት ወዲህ ዋንጫው ከአውሮፓ ሲወጣ ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው።

የፈረንሳዩ ዕምቤፔና የአርጀንቲናው ሜሲ ሁለቱም በውድድሩ ወቅት ለቡድናቸው አምስት - አምስት ግቦችን አስቆጥረዋል።
በዓለም ዋንጫው ውድድር ልዩ ብቃት ካስመዘገቡት ውስጥ የፈረንሳዩ ሉዊዝ ፈረናንዴዝ ከአራት ዓመት በፊት ዕምቤፔ ተሸልሞ የነበረውን የውድድሩ ኮከብ ወጣት ተጫዋች ሽልማት አግኝቷል።
የአርጀንቲናው እሚሊአኖ ማርቲኔዝ የወርቅ ጓንት ሲያገኝ በውድድሩ ወቅት ስምንት ግቦችን ያስቆጠረው ዕምቤፔ የወርቅ ጫማ ተሸላሚ ሆኗል።

የአርጀቲናው ሜሲ በውድድሩ ምርጥ ተጫዋችነት ወርቅ ኳስ ለመሸለም በቅቷል።
ከግጥሚያው በፊት በርችት በደመቀው የሉሴይል ስታዲየም የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ የኳታር ገጣሚ አይሻ፣ አሜሪካዊ ናይጄሪያዊ ዳቪዶ፣ የፖርቶሪኮ ሬጋቶን ዘፋኝ ኦዙና፣ የፈረንሳይ ራፐር ጂምስ፣ ሞሮካዊ ካናዳዊ ድምፃዊት ኖራ ፈቲሂ፣ ኢሚራቲ ፖፕ ኮከብ ባልቀስ፣ የኢራቅ ሙዚቀኛ ራህማ ሬድና የሞሮኮ ድምፃዊ ማናል ተገኝተው ለስንብቱ ልዩ ዝግጀት ድምቀትን አላብሳዋል።

አርጀንቲና የ2022 የዓለም ዋንጫ ባለቤት በመሆን ለሶስተኛ ጊዜ አሸናፊ በመሆኗ፤ ለአምስት ጊዜያት የዓለም ዋንጫ ባለቤት ከሆነችው ብራዚልና ለአራት ጊዜ አሸናፊ ከሆነው ገርመን ቀጥላ በሶስተኛ ደረጃ እንድትመዘገብ አድርጓታል።

