የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በቀድሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝደንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል፡፡
ምክር ቤቱ ባወጣው የሐዘን መግለጫ "የሀገራችን ዋርካ እና የሁሉም አባት የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ባጋጠማቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ወደ አኼራ ሔደዋል" ብሏል::
"ሕልፈታቸው የመላው ሀገራችን ሕዝብ ሐዘን ነው" ሲልም ምክር ቤቱ አክሎ ገልጿል፡፡
ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ ላበርክቷቸው ሀገራዊና ሃይማኖታዊ አስተዋፆ በሚመጥን መልኩ ሥርዓተ ቀብራቸው በመንግሥት ደረጃ እስላማዊ ሥነ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን በመውሰድ እንደሚፈፀምም አስታውቋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው "የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጂ ዑመር ኢድሪስ በማረፋቸው ሐዘን ተሰምቶኛል ። ሐጂ ዑመር በአመራር ዘመናቸው የተለያዩ ወገኖች ወደ አንድነት እንዲመጡ እና የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሕግ ዕውቅና እንዲኖረው ያደረጉትን አስተዋጽዖ ሁሌም እናስታውሰዋለን" ብለዋል።

