የቪክቶሪያ መንግሥት ከአንድ ሺህ በላይ ታዳሚዎች ለ100ኛ ጊዜ በሚካሄደው የሜልበርን ኮኦክስ ፕሌት የፈረስ ውድድር እንዲገኙ ቸሮ የነበረውን ይሁንታ ከማኅበረሰብ አባላት በደረሱበት ብርቱ ትችቶች ሳቢያ መልሶ አጥፏል።
ትናንት ከቀትር በኋላ የቪክቶሪያ መንግሥት ሙኒ ቫሊ ዓርብ ምሽት በሚካሄደው ማኒካቶ ስቴክስና በቅዳሜው ኮኦክስ ፕሌት የፈረስ ውድድሮች ላይ ከፈርስ ጋላቢዎች፣ ሠራተኞች፣ የሚዲያና ጸጥታ ሠራተኞች በተጨማሪ 500 ባለቤቶችና ግንኙነት ያላቸው በጥቅሉ ከ 1,250 ያልበለጡ ሰዎች በውድድር ሥፍራዎቹ እንዲገኙ ፈቃድ መስጠቱን አስታውቆ ነበር።
ሆኖም በማኅበራዊ ሚዲያ በቀብርና በቤተሰብ ጥየቃዎች ላይ ገደብ ተጥሎ ለፈረስ እሽቅድምድም ከሺህ በላይ ሰዎች እንዲታደሙ መፍቀድ አግባብነት የሌለው መሆኑን በማመላከት ከማኅበረስብ አባላት በተሰነዘሩ የሰሉ ትችቶች አስባብ የውድድር ሚኒስትር ማርቲን ፓኩላ ውሳኔያቸውን ማጠፋቸውን ዛሬ አስታውቀዋል።
"ባለቤቶቹ የሚቀጥለው የገደብ መላላቶች ደረጃ ላይ እስከምንደርስ ድረስ ወደ ውድድር መስክ አይገቡም። ውሳኔው ላስከተለው ብስጭት ይቅርታ እጠይቃለሁ"
"ተጥለው ካሉት ገደቦች አኳያ ያን መወሰኑ ስህተት ነበር፤ የማኅበረሰቡን የአጸፋ ምላሽ አድምጠናል" በማለት ከይቅርታ ጋር ውሳኔያቸውን ማንሳታቸውን ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ባለፉት 24 ሰዓታት ቪክቶሪያ ውስጥ ሶስት ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲያዙ አንድም ሕይወት ሳያልፍ ቀርቷል።
የቪክቶሪያ የ14 ቀናት አማካይ የኮሮናቫይረስ ተዛማችነት 6.2 ሲደርስ የሪጂናል ቪክቶሪያ 0.4 ሆኗል።
ምንጩ ያለየ የቫይረስ ቁጥር ባለፉት 24 ሰዓታት ከ13 ወደ 10 ወርዷል።
ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 817 ላይ ረግቷል።
ቫይረስ ኒው ሳዝ ዌይልስ
የኒው ሳውዝ ዌይልስ መንግሥት በእምነት ቤቶች ላይ ተጥለው የነበሩ የኮሮናቫይረስ ገደቦችን አላላ።
የስቴት ባለስልጣናት ከፊታችን ዓርብ ኦክቶበር 23 ጀምሮ ምዕመናን በየቤተ እምነት ቤታቸው እስከ 300 ሰዎች ሆነው የጸሎት ሥነ ሥርዓት መከታተል እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ተመርማሪዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣትን ተከትሎ የጤና ሚኒስትር ብራድ ሃዛርድ ግለሰቦች መመርመር ሲኖርባቸው ቸል እንዳይሉ በማሳሰብና በማበረታት ሲናገሩ፤
" የኛን ጊዜ እያባከናችሁ አይደለም። ለራሳችሁና ለማኅበረሰቡ መልካም ነገርን እያደረጋችሁ እንጂ። ሂዱና ተመርመሩ። እናንት ኮቨድ - 19ን በመፋለሙ ረገድ ከመጀመሪያው ግንባር መስመር ተሰልፋችሁ ያላችሁ ናችሁ። ሁላችንም። አጋዥ እንድትሆኑን እሻለሁ" ብለዋል።