የቪክቶሪያ ተቃዋሚ ቡድን መሪ ብራድ ባቲን በቪክቶሪያ ፓርላማ የሊብራል ፓርቲ መሰብሰቢያ አዳራሽ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ የፓርቲያቸውን የቤት፣ የንግድ፣ ጋዝና ትምህርት ፖሊሲ አብራርተዋል።
አቶ ባቲን በጋዜጣዊ መግለጫቸው የፓርቲያቸውን ፖሊሲዎች ሲያስረዱ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ አንድ ሚሊየን የሚያወጣ ቤት ለሚገዙ የቪክቶሪያ ነዋሪዎች የመሬት ግብር እፎይታ በመስጠት 55 ሺህ ዶላር ያህል እንዲቆጥቡ የሚያስችላቸው መሆኑን ገልጠዋል።
በቂና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ለቪክቶሪያ ነዋሪዎች ለማዳረስ የጋዝ ፍለጋና አቅርቦት እንዲካሔድ፣ እንዲሁም በግልና የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ክፍያ ለከፍተኛ ጫና ለተጋለጡ ወላጆች ወጪያቸው እንዲቃለል ለማድረግ ውጥን ያለው መሆኑን ተናግረዋል።
የተቃዋሚ ቡድኑ የመድብለባሕል ጉዳዮች ቃል አቀባይ ኢቫን ማልሆላንድ በበኩላቸው ቀደም ሲል በቪክቶሪያ የላይኛው ምክር ቤት ምዕራብ ሲድኒ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳብ ፤ የፌዴራል መንግሥቱ ሲድኒ ላይ ሁለተኛ የSBS ስርጭት ማዕከል ለማቆም ውሳኔ ማሳለፉና ሙጥኝ ማለቱ ከፖለቲካ ትርፍ አኳያ እንደሁ አመላክተዋል።
አቶ ማልሆላንድ አያይዘውም፤ "ቪክቶሪያ የአውስትራሊያ መድብለባሕል መዲና ናት፤ SBS ያን ሊያንፀባርቅ ይገባል"
"ቪክቶሪያ ከኒው ሳውዝ ዌይልስ የላቀ የባሕር ማዶ ተወላጆች አሏት"
እናም " ሁሉንም አውስትራሊያውያን ሊወክል ይገባል፤ አለያ የሲድኒ ስርጭት አገልግሎት ብቻ ሆኖ የቀራል" ብለዋል።
ስለሆነም "ወደ ሜልበርን ሊዛወር ይገባል" ሲሉ የሊብራል ናሽናልስ - አቋም አንፀባርቀዋል።