በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት መካከል ዛሬ ይጀመራል ለተባለው የሰላም ንግግር የሁለቱም ወገኖች ተደራዳሪዎች ደቡብ አፍሪካ መግባታቸው እየተሰማ ነው።
ምንም እንኳ ድርድሩ የሚካሄድበት ትክክለኛ ቦታና ሰዓት በጥብቅ ምሥጢር የተያዘና እስካሁንም ያልተገለፀ ቢሆንም የሕወሓት የውጭ ጉዳዮች ቢሮ ቃል አቀባይ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት በፃፉት የትዊተር መረጃ ተደራዳሪዎቻቸው ደቡብ አፍሪካ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
“በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው የኢትዮጵያ ትግራይ የሠላም ንግግር ላይ ለመገኘት ልዑካን ቡድናችን ደቡብ አፍሪካ ገብቷል” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም “ውጊያው ፈጥኖ እንዲቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትና የኤርትራ ኃይሎች መውጣት” ላይ ቅድሚያ አጀንዳቸው መሆኑን ገልፀዋል።
ከህወሓት ተደራዳሪዎች መካከል ጄነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ እና አቶ ጌታቸው ረዳ እንደሚገኙበት የታወቀ ሲሆን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል በይፋ ባይገለፅም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቴዎስና ዶ/ር ጌታቸው ጀምበር ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸውን ምንጮች ጠቆሙ።
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]