የኒው ሳውዝ ዌይልስ ሌበር ፓርቲ ራሱን ችሎ አብላጫ ወንበር ያለው መንግሥት ለማቆም የሚያስችሉትን 47 የምክር ቤት ወንበሮች በእርግጥኝነት እንደሚያገኝ የተጠቆመ ሲሆን፤ ከቶውንም የድምፅ ቆጠራው ሲያበቃ እስከ 50 የምክር ቤት ወንበሮችን ሊያሸንፍ እንደሚችል በABC የምርጫ ተንታኝ ተገምቷል።
በሌላ በኩል የቀድሞው የሊብራል ፓርቲ መሪና የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፕሪሚየር ዶሜኒክ ፔሮቴይ ፓርቲያቸው በምርጫው ድል ለመነሳቱ ሙሉ ኃላፊነትን እንደሚወስዱ ገልጠው፤ ያም በመሆኑ በፈቃዳቸው ከሊብራል ፓርቲ መሪነት ራሳቸውን ማግለላቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ፔሮቴይ ለመሪነት የበቁት በፀረ ሙስና ኮሚሽን ለምርመራ ግድ በመሰኘታቸው ከስልጣናቸው በተሰናበቱት የቀድሞዋ የሊብራል ፓርቲ መሪና ፕሪሚየር ግላዲስ በርጂክሊያን እግር ተተክተው ነው።
ሲመለከቱት የነበረውን የእግር ኳስ ጨዋታ አቋርጠው የሌበር የድል ብስራት መታደሚያ በሆነው አዳራሽ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ
"የኒው ሳውዝ ዌይልስ ሕዝብ በጋራ ሆኖ የተሻለ መፃኢ ጊዜን መርጧል። በዛሬዋ ምሽት የኒው ሳውዝ ዌይልስ አዲስ ጅማሮ ይጀመራል... የሚጀምረውም በታላቅ መሪ ነው" ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ በታላቅ መሪነት የተወደሱት አዲሱ ተመራጭ 47ኛው የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፕሪሚየር ክሪስ ሚንስ የኒው ሳውዝ ዌይልስ ሕዝብ ሌበርን ለመንግሥትነት በማብቃቱ ለስኬት እንጂ ለክሽፈት እንደማይዳርጉት ተናግረዋል።
የሌበር ፓርቲ ቀደም ሲል ከሁለኛው ጦርነት በኋላ ከተቃዋሚነት ተነስቶ ለመንግሥትነት የበቃው በ1976 በኔቪል ራን እና በ1995 በቦብ ካር መሪነት ነው።

