በመላ አውስትራሊያ ዋና ዋና ከተሞች በየዓመቱ ጃኑዋሪ 26 የሚከበረውን የአውስትራሊያ ቀን በወረራ ቀን በመፈረጅ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ምንም እንኳ ከ1938 አንስቶ በአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ዘንድ የአውስትራሊያ ቀን በ 'ወረራ' እና 'የሐዘን' ቀንነት አስመልክቶ በየዓመቱ ተቃውሞ ማሰማትና በነባር ዜጎችና በፍልስጤማውያን መካከል የትግል አጋርነት ማሳየት የቆየ ቢሆንም፤ አራት ወራት ባስቆጠረው የጋዛ - እሥራኤል ጦርነት ሳቢያ በ2024 ማዕከላዊ ሥፍራን ይዟል።
የአፓላዋ ሰውና አንቂ ማይክል ማንሴል "ጋዛ ውስጥ የሚሆነውና እዚህ አውስትራሊያ ውስጥ በነባር ዜጎች ላይ የሚሆነው የመሬት ነጠቃዎች በመላው ዓለም ለጋራ የትግል አጋርነት አስባብነት ረብ ያለው ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የዓመቱ አውስትራሊያውያን
ፕሮፌሰር ጆርጂና ሎንግ እና ፕሮፌሰር ሪችድ ስኮልየር በጣምራ የ2024 የዓመቱ አውስትራሊያውያን ተብለው ተሰየሙ።
ፕሮፌሰሮቹ ስኮልየር እና ሎንግ በኢሙዩኖሕክምና ሜላኖማን በማከም በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ለመታደግ የቻሉ ናቸው።
ሁለቱ ፕሮፌሰሮች በአሁኑ ወቅት በምርምር ሥራቸው ለአዕምሮ ካንሰር መፈወሻ ለማግኘት እየጣሩ ናቸው።