በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ራሳቸውን ለኢትዮጵያውያን - አውስትራሊያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዛሬ ኤፕሪል 27 ከምሽቱ 8:00 pm ጀምሮ በተዘጋጀው የበይነ መረብ የትውውቅ መድረክ ላይ አስተዋውቀዋል።
የትውውቅ መድረኩን ያዘጋጀው በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሲሆን፤ በትውውቅ መድረኩ የተጋበዙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንንም ራሳቸውን በየተራ አስተዋውቀዋል። የ 'እንኳን ደህና መጡ' እና 'መልካም የሥራ ዘመን' ምኞታቸውንም ገልጠዋል።
የትውውቅ መድረኩን የመሩት አቶ በሪሁን ደጉ - በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትርና ምክትል ሚሽን መሪ፤ የአዲሱን አምባሳደር የትምህርት፣ የመንግሥታዊ ሥራና ኃላፊነት ደረጃዎች ሲጠቅሱ፤
- በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር
- የጠቅላይ ሚኒስትር የካቢኔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር
- በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የሪፎርም፣ የመልካም አስተዳደርና የሲቪል ሰርቪስ ዘርፍ አስተባባሪ
- የኦሮሚያ ብሐራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚደንት
- በጠ/ሚ/ር ጽሕፈት ቤት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመልካም አስተዳደርና የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር
- በኦቶዋ ካናዳ የኢፌዴሪ ኤምባሲ በባለ ሙሉ ስልጣን ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚና ቢዝነስ ዘርፍ ኃላፊ
በመሆን እንዳገለገሉና በደቡብ ኮሪያ ዮንሲ ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን እንዳገኙ ተናግረዋል።
አምባሳደር ሙክታርም በንግግራቸው መጀመሪያ የትውውቅ መድረኩን ላዘጋጁት የኤምባሲ አባላትና ጥሪውን አክብረው ለተገኙ የማኅበረሰብ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
አያይዘውም፤ አውስትራሊያ ውስጥ በኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵውያን እየተካሄዱ የነበሩትን እንቅስቃሴዎች በአምባሳደርነት ከመመደባቸው በፊት ይከታተሉ እንደነበርና ከምደባቸው በኋላም የቅርብ ትኩረት መስጠታቸውን ጠቁመዋል።

Source: SBS Amharic
በሂደቱም ኢትዮጵያውያን - አውስትራሊያውያን አገራቸው በፈለገቻቸው ግንባሮች በአለኝታነት ማገልገላቸውን የተገነዘቡ መሆኑን በመጥቀስ "ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲከሰት ለልጆቿ ጥሪ ባደረገችበት ወቅት፣ የሕዳሴ ግድብንና ገበታ ለአገርን አስመልክቶ ያደረጋችሁት አስተዋፅዖዎች በገንዘብ የሚተመኑ አይደሉም። የመከላከያ ሠራዊታችን ከጀርባው በተወጋበት ወቅት ከሕዝባችንና ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሰለፍ ሚናችሁ የጎላ ነበር። እንዲህ ያለ አገራዊ ፍቅር ካላቸው የዳያስፖራ አባላት ጋር በመገኘቴ ታላቅ ዕድል ይሰማኛል" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ገጥሟት ያለውን የወቅቱን ፈተናዎች አስመልክተ ሲናገሩም " በአሁኑ ወቅት የተደቀነው አደጋ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈትን ነው። ታሪካዊ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ የደከመች ወይም የተበተነች እንድትሆን ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉበት ወቅት ነው" በማለት አስገንዝበዋል።
በአውስትራሊያ ነዋሪ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት የአንድነት ጥሪ ሲያቀርቡም "አገር ኖሮን መወቃቀስ ክብር ነው። ለልዩነቶች ጊዜ ይኖረናል። አገር ያለው ሰው ክብር አለው። የተለያዩ አስተሳሰቦች፤ ፖለቲካዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ አገራችንን ወደፊት ከማሻገር አኳያ አንድ ሆነን በአንድነት እንድንሸጋገር ነው ጥሪ የማደርግላችሁ። ኤምባሲው የእናንተ ነው። የኢትዮጵያ አቅም እናንተ ናችሁ" ብለዋል።