በአውስትራሊያ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በጦርነት ሳቢያ ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን መርጃ የሚውል በዛሬው ዕለት ባካሔዱት የዙም ስብሰባ $178,000 አሰባስበዋል።
የዕለቱን ስብሰባ ያዘጋጀው "ኢትዮጵያን እናድን" አስተባባሪ አቶ አያሌው ሁንዴሳ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር "ከሰባት ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው በሚገኙበት ወቅት እኛ ልጆቿ የድርሻችንን ልንቸር ይገባናል" ብለዋል።
በዕለቱ ተጋባዥ ከነበሩ ሶስት እንግዶች ውስጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ "በውጭ የምትገኙ ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባችሁን ለማድረግ ወደ ኋላ እንደማትሉ እርግጠኛ ነኝ። በ2013 - 14 የዳያስፖራው ማኅበረሰብ እንደ ዲፕሎማት አገሩን ያገለገለበት፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ አገሩን ያገዘበትና በፖለቲካ ጫናውም እገዛ ያደረገበት ዓመት ነው።
"በጦርነት ተፈናቅለው ጧሪያቸውን ያጡ፣ ገቢያቸውንና ሥራቸውን ያጡ ብዙ ናቸው። ይኼ ማኅበራዊ ቀውስ ከጦርነቱ በላይ አገር ሊጎዳ የሚችል ነው። ርቀት በአገር ጉዳይ ላይ ቁልፍ ሚና ከመጫወት እንደማይገድብ ማረጋገጫ ነው። የፈረሱ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት መልሰው መቋቋም አለባቸው። በጋራ ገንብተው፣ በጋራ ገንብተን፣ በጋራ የምንኮራባት አገር እንድትኖረን የእናንተን ርብርብ እጠይቃለሁ" ሲሉ ተናግረዋል።

Ayalew Hundessa. Source: SBS Amharic

Dr Mohammed Edris. Source: SBS Amharic
ከእሳቸው ቀደም ብለው ተጋባዥ ተናጋሪ የነበሩት አቶ ነዓምን ዘለቀ "ከውጭ ያላችሁና በዚህ የታደማችሁ ኢትዮጵያ ከእናንተ የምትጠብቀው አለ። በርካታ ተፈናቃዮች አሉ። ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ የሚገኘው ገቢ በጣም ወሳኝና ጠቃሚ ነው። የታደማችሁበት ዝግጅት እንዲሳካ እመኛለሁ። የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ" ብለዋል።
ሶስተኛው ተጋባዥ ተናጋሪ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ካሣዬ ጨመዳ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ ልጆች አሏት። እናንተ አላችሁ። ተመልሳችሁ የምትገቡባት አገራችሁ ናት። ለኢትዮጵያ በችግሯ ቀን ይህን አድርጌላታለሁ ብላችሁ የኅሊና እርካታ የምታገኙባእት ነው" በማለት ተናግረዋል።