የኒጄር ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ደጋፊዎች በመዲናይቱ ኒአሜይ የሚገኘውን የገዢው ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት በእሳት አጋይተዋል።
የኒጄር ፕሬዚደንት መሐመድ ባዙም እስካሁን በመፈንቅለ መንግሥት ፈፃሚዎቹ እግት ስር ያሉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስና የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፕሬዚደንቱ ከእገታ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ካሪን ዤን-ፒየር ኒጄር ዩናይትድ ስቴትስ ሁኔታውን ኒጄር በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል እየተከታተለች እንደሁ ጠቅሰው እዚያ የሚገኙ አሜሪካውያን ከፍ ያለ ጥንቃቄን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
አያይዘውም "እኛ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠ ፕሬዚደንት ጠንካር ድጋፍ እሰጣለን፤ በመሆኑም ስልጣንን በኃይል ለመያዝ የሚደረግ ማናቸውንም ዓይነት ጥረት በብርቱ እናወግዛለን" ብለዋል።
የሴቶች እግር ኳስ የዓለም ዋንጫ
ትናንት ሐሙስ ምሽት በአውስትራሊያ ማቲልዳስና በናይጄሪያ ሱፐር ፋልከንስ ብሔራዊ የሴቶች እግር ኳስ ቡድናት መካከል በተካሔደው ግጥሚያ የማቲልዳስ በሱፐር ፋልከንስ 3 ለ 2 መረታት፤ የዋንጫ ባለቤት ይሆናሉ ተብለው ትልቅ ተስፋ በተጣለባቸው የማቲልዳስ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች ላይ ብርቱ ተፅዕኖ አሳድሯል።

አውስትራሊያ ሰኞ ሐምሌ 24 / ጁላይ 31 የመጨረሻ የምድብ ማጠናቀቂያ ግጥሚያዋን ከካናዳ ታደርጋለች።

አውስትራሊያ ለቀጣዩ የጥሎ ማለፍ ውድድር ከምድቧ አላፊ ከሚሆኑት ሁለት ቡድናት ውስጥ አንዷ ሆና ለማለፍ ግጥሚያውን የግድ በአሸናፊት መፈፀም ይጠበቅባታል።


