በዓመታዊው የ2025 ወርኃ ጁላይ ይፋ ሉላዊ የፓስፖርት ደረጃ ምደባ ሠንጠረዥ መሠረት ሲንጋፖር የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተመድባለች።
ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ የሁለተኛነት ሥፍራን ይዘዋል።
አውስትራሊያ አምና ከነበረችበት ስድስተኛ ደረጃ ዝቅ ብላ ሰባተኛ ረድፍ ላይ ተገኝታለች።
የእንግሊዝ ፓስፖርት 6ኛ፣ የዩናይትድ ስቴትስ 10ኛ፤ የቻይና 60ኛ የደረጃ ሠንጠረዥ ውስጥ ተካትተዋል።
የናይጄሪያ ፓስፖርት ከኢትዮጵያ ፓስፖርት እኩል 88ኛ ላይ ሲገኝ፤ የኤርትራ ፓስፖርት 94ኛ የደረጃ ሠንጠረዥ ውስጥ ተቀምጧል።
የሠንጠረዡ መጨረሻ ላይ በ99ኛ ደረጃ የተጠቃለለችው አፍጋኒሲታን ሆናለች።
ሉላዊ የፓስፖርት ደረጃ ምደባ የተጀመረው ከ20 ዓመታት በፊት ነው።
ከዋነኛ ደረጃ ምደባ መመዘኛዎቹ ውስጥ አንዱ ባለ ፓስፖርት ተጓዦች ወደ አንድ ሀገር ለመግባት ያለ ቪዛ ወይም የመዳረሻቸው ሀገር ላይ እንደደረሱ የመግቢያ ቪዛ ማግኘት መቻላቸው ነው።
በደረጃ መዳቢው ሄንሊይ እና ሽርካዎቹ ሊቀመንበር ዶ/ር ክርስቲያን ካሊን፤ ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ውስጥ የዓለም አቀፍ ጉዞ ተደራሽነት መሻሻል እንዳሳየ ጠቅሰዋል።
አክለውም "በአማካይ የተጓዦች ከቪዛ ነፃ ተጠቃሚነት በ2006 ከነበሩት 58 መዳረሻዎች በ2024 ወደ 111 ከፍ ብለዋል። ሆኖም ሁሉም ፓስፓርቶች ጠቀሜታቸው እኩል አይደለም" ብለዋል።