የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤቱ ንጉሠ ነገሥቱ ሕይወታቸውን ያጡበት ኦገስት 27 / ነሐሴ 21 ቀን በመዘከር ባወጣው መግለጫ፤
"የማይታረቁ የሚመስሉ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ንጉሠ ነገሥቱ በእምነት፣ በዲሲፕሊን እና በፅናት በመታገል ለሀገራቸው ዘመናዊነትን ለማምጣት ጥረት በማድረግ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ባርነት ነፃ ለማውጣት ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል" ሲል የአፄ ኃይለ ሥላሴን ሀገራዊና አኅጉራዊ ሚና አመላክቷል።
አያይዞም፤ የጣሊያን ፋሽስት የአምስት ዓመት የወረራ ጊዜ የስደት ሕይወታቸውን በማውሳት፤
"ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሠርተዋል። ብልህ የፖለቲካና የአመራር ብቃታቸውን ተጠቅመው ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ነፃ አውጥተዋል። የስደት ሸክሙ፣ ኪሳራና ብቸኝነት ቢኖረውም፤ እነዚህን የጭቆና ዓመታት አሸንፈው ስለ መጪው ጊዜያት ለማሰላሰል ተጠቅመውበታል" በማለት አመላክቷል።

Haile Selassie I (previously Prince Ras Tafari), (1891 - 1975), Emperor of Ethiopia, addresses the General Assembly of the United Nations on October 7, 1963, in New York City, New York. Credit: Michael Ochs Archives/Getty Images
"ለትምህርት ትኩረት በመስጠት የኢትዮጵያን ልማት የሚመራና የሚረዳ የተማረ ክፍል ገንብተዋል። በግብርና፣ በትምህርት እና በኢንዱስትሪ ማስፋፋት ትልቅ እመርታን አሳይተዋል። ዘመናዊ የምድር ጦር፣ አየር ኃይል እና ባሕር ኃይልንም መገንባት ችለዋል" ያለ ሲሆን፤ እኒህም የተከወኑት በመከፋፈልና የውስጥ ግጭቶች ውስጥ ተፈትኖ ለስኬት የበቃ እንደነበር አውስቷል።
የዘውድ ምክር ቤቱ መግለጫ ያለፉትን 50 ዓመታት በመዳሰስ፤ ከንጉሠ ነገሥቱ ከዙፋን መነሳትና ሕይወታቸውም በሰው እጅ ማለፍን ተከትሎ ባለፉት አምስት አሠርት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ብርቱ ችግሮች ነቅሷል።
"ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ በሕግ፣ በውክልናና በተጠያቂነት ላይ የተመሰረተ ሥርዓት መፍጠር ተስኖናል። ከታሪካችን ጋር መታረቅ ተስኖናል። ለሕዝባችንና ለሀገራችን የመረጋጋት ርዕይ መቅረፅ ተስኖናል፤ ኢትዮጵያ በሙሉ ልብ ወደፊት አሻግራ እንድታይ የሚያስችል ርዕይ እነሆን ማለት ተስኖናል።
"ኢፍትሐዊነትን ለመዋጋት፣ አፍሪካን ነጻ ለማውጣት እና አፍሪካውያንን በዓለም መድረክ ድምፅ የማሰማት ሥራቸው በታሪክ ውስጥ ተቀርጿል። ለተጨቆኑ ሰዎች ተስፋ ሰጥተዋል። በዓለም ዙሪያ የጥቁር ኩራት ምልክት ሆነዋል። በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አማካኝነት የመላው አኅጉር አባት ለመሆን በቅተዋል፤ በራስተፈሪያን አማካኝነት ሉላዊ የጥቁር የነፃነት ንቅናቄ መንፈስን አነሳስተዋል።

Haile Selassie (1892-1975), the Emperor of Ethiopia, opens the conference of the Organisation of African Unity in Addis Ababa, Ethiopia, on 6 February 1973. Credit: William Lovelace/Express/Hulton Archive/Getty Images

HIH Prince Ermias Sahle Selassie Haile Selassie, President of the Crown Council of Ethiopia. Credit: Crown Council of Ethiopia