ሄንሪ ኪሲንጀር ከ1973 እስከ 1977 በፕሬዚደንት ሪቻርድ ኒክሰንና ፕሬዚደንት ጄራልድ ፎርድ አስተዳደር የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሠርተዋል።
በጀርመን ከይሁዳውያን ቤተሰብ የተወለዱት ኪሲንጀር በአሜሪካ የውጭ ፖሊሲና በቀዝቃዛው ጦርነት ዓለም አቀፍ ግንኙነት ግዙፍ አሻራቸውን አሳርፈዋል።
በአንድ ወገን የዓለም አቅፍ ዲፕሎማሲ ጠቢብ ተብለው ሲወደሱ፤ በሌላ በኩል በጦር ወንጀለኝነት ይኮነናሉ።
በ1973 የኖቤል ሰላም ሽልማት ተቀባይ ሲሆኑ፤ በወቅቱ ሁለት የሽልማት ኮሚቴው አባላት ተቃውሞ አሰምተው ከኖቤል ሰላም ሽልማት ኮሚቴ አባልነታቸው ለቅቀዋል።
አብረዋቸው በጣምራ ሽልማቱን እንዲቀበሉ የተጠሩት የሰሜን ቬትናሙ ሊ ዳክ ቲሆም በበኩላቸው የኖቤል ሰላም ሽልማቱን ከኪሲንጀር ጋር አልጋራም ብለው ቀርተዋል።
"በልህቀት የተመላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር"ሲሉ ያሞኳሻቸው የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ጄራልድ ፎርድ "ሄንሪ ከቶውንም እራሱን ስሕተት የሚሠራ አድርጎ አይመለከትም፤ ከማውቃቸው የሕዝብ አገልጋዮች ሁሉ ቆዳው ስስ ነው" ሲሉ ገልጠዋቸዋል።
ሄንሪ የአሜሪካና ቻይናን የወዳጅነት በር በመክፈት ይታወሳሉ። በ2023 ጁላይ ወደ ቻይና ተጉዘው የፕሬዚደንት ሺ ጂንፒንግ እንግዳ ለመሆን በቅተዋል።
ሄይንዝ አልፍሬድ ኪሲንጀር፤ ፈርዝ - ጀርመን የተወለዱት ሜይ 27,1923 ሲሆን በ1943 የአሜሪካ ዜግነትን አግኝተዋል። ስማቸውንም ወደ ሄንሪ ኪሲንጀር ለውጠዋል።
ሄንሪ ኪሲንጀር በ1952 ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በ1954 ሶስተኛ ዲግሪያቸውን ከሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አግኝተተዋል።