ቪክቶሪያ ባለፉት 24 ሰዓታት የሶስት ነዋሪዎቿን በኮሮናቫይረስ መያዝ ተከትሎ ከዛሬ ከምሽቱ 5፡00 pm ጀምሮ አዲስ የኮሮናቫይረስ ገደቦችን መጣሏን ተጠባባቂ ፕሪሚየር ጃሲንታ አለን አስታወቁ።
በዚህም መሠረት፦
- በግለሰብ መኖሪያ ቤት እስከ 30 መሰባሰብ ይፈቀድ የነበረው ወደ 15 ዝቅ ብሏል
- የፊት ጭምብሎችን በቤቶች ውስጥ ማጥለቅ ግዴታ ሆኗል። ከቤትዎ ለመውጣት ሲያቅዱ የፊት ጭምብል ይዘው ይውጡ፤ ሲመገቡና ሲጠጡ ካልሆነ በስተቀር ከግል መኖሪያዎ ውጪ በማናቸውም የቤት ውስጥ ሁነት ሲታደሙ የፊት ጭምብል ማድረግ ይጠበቅብዎታል። ከገደቡ ጋር ተያይዞ መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞቻቸው በቢሮ የሥራ ገበታቸው ላይ ሲገኙ ጭምብሎችን እንዲያጠልቁ መመሪያዎችን ማስተላለፍ ጀምረዋል።
- አስቀድመው ያስያዙት ጉዳይ ከሌለዎት ወደ ከተማ አይሂዱ
- በቤት ውስጥ ሁነት የፊት ጭምብል ያጥልቁ
- መልካም የእጅ ሥነ ንጽሕናን ይተግብሩ
- ሕመም ከተሰማዎት ቤትዎ ይቆዩ
ለአዲሱ ገደብ መጣል አስባብ የሆኑትና ወሸባ እንዲገቡ ግድ የተሰኙት ሶስት ሴቶች የቫይረስ ጥቃት ከሲድኒ ከተከሰተው ኮሮናቫይረስ ጋር የተገናኘ ነው ብሎ የቪክቶሪያ መንግሥት ያምናል።
አንደኛዋ የቫይረሱ ተጠቂ ሴት ዕድሜያቸው በ70ዎቹ ውስጥ ያለ ሲሆን፤ ሌሎቹ ሁለቱ ሴቶች በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ናቸው። መኖሪያችውም በሜልበርን ሚትቻም፣ ሃላምና ሜንቶን ቀበሌዎች ናቸው።
ቪክቶሪያ ያለ አንዳች የማኅበረሰብ ቫይረስ ተጋቦት 60 ቀናትን በተከታታይ አስቆጥራለች።
በሌላ በኩል ባለፉት 24 ሰዓታት ኒው ሳዝ ዌይልስ ውስጥ 10 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ተጠቅተዋል።
በጥቅሉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 144 ደርሷል።