በመላው ፐርዝ ከተማ ከዛሬ ጃኑዋሪ 31 ከምሽቱ 6 ሰዓት (6pm) ጀምሮ ለአምስት ቀናት ፀንቶ የሚቆይ የኮረናቫይረስ ገደቦች ተጥለዋል።
ለገደቦቹ መጣል አስባብ የሆነውም አንድ 20ዎቹ ውስጥ ያለ የሆቴል ወሸባ የጥበቃ ሠራተኛ ብርቱ በሆነው የእንግሊዝ ተሠራጭ ኮሮናቫይረስ (UK variant) መያዝ ነው።
በጥበቃ ሥራ የተሰማራው ግለሰብ አንድ በዚሁ ቫይረስ የተያዘ ግለሰብ ባለበት የሆቴል መተላለፊያ ይሠራ ነበር።
ይህንኑ ተከትሎ የመስተንግዶ ግልጋሎት መስጫዎች፣ መጠጥ ቤቶችና ክለቦች፤ የአካል ማጠንከሪያና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ የመጫዎቻ ቦታዎችና የእምነት ቤቶች ዝግ ይሆናሉ።
በነገው ዕለት ይከፈቱ የነበሩ ትምህርት ቤቶችም ለአምስት ቀናት ዝግ ሆነው ይቆያሉ።
ሆኖም፤ ምግብ ቤቶችና ካፌዎች በቁማቸው ለሚያዙ ደንበኞች ግልጋሎቶቻቸውን ለመስጠት ክፍት ሆነው ይቀጥላሉ።
የቀብር ሥነ ሥርዓት ከ10 ባልበለጡ ለቀስተኞች የሚካሄድ ሲሆን፤ በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ውስጥ የሠርግ ሥነ ሥርአቶችን ማካሄድ አይቻልም።
የአረጋውያን መጠወሪያ ቤቶችን ልዩ ሁኔታ ካልገጠመ በስተቀር መጎብኘት አይፈቀደም።
የፐርዝ ነዋሪዎች ከቤት ለመውጣት የሚችሉት አስፈላጊ ነገሮችን ከገበያ ለመሸመት፣ ለሕክምና ወይም ለጤና ክብካቤና የረድኤት ተግባራትን ለማከናወን፣ ከአንድ ተጨማሪ ግለሰብ ጋር ከቤትና ጎረቤት ባልራቀ የአንድ ሰዓት የአካል እንቅስቃሴ ለማድረኛ ከቤት ሆኖ ለመሥራት የማይቻል ከሆነ ወደ ሥራ ለመሰማራት ይሆናል።
የምዕራብ አውስትራሊያ ፕሪሚየር ማርክ ማክጋዋን ነዋሪዎች የሕዝብ ትራንስፖርት ሲጠቀሙ ጭምብል የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸው ሁሉ ለማንኛውም ምክንያት ከቤት ሲወጡም ጭምብል ማድረግ እንደሚጥጠበቅባቸው አስታውቀዋል።