የአማራ ክልል ፕሬዜዳንት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ፤ የሚያጋጥሙንን የፖለቲካ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የአማራ እና የትግራይን ህዝብ ወንድማማችነት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እንሰራለን አሉ።
ይህን ያሉት ለክልሉ ሚዲያ አሚኮ በሠጡት ቃለ ምልልስ ነው።
ዶ/ር ይልቃል ፥ የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ወደ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በማሳደግ ተደጋግፈን ከችግራችን የምንወጣበትን መንገድ ማመቻቸት አለብን ብለዋል።
" የፖለቲካ ልዩነትን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን አማራጭ ማድረግ መፍትሄ አልባ ኪሳራ እንደሚያደርስ አስተምሮናል " ያሉት ዶ/ር ይልቃል ቀድሞውኑ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ተፈተው ቢሆን ፣ በውይይት እና ድርድር ተፈተው ቢሆን ፣ በሽምግልናና በሰለጠነ አግባብ ተፈተው ቢሆን ይህ ሁሉ ችግር እና ምስቅልቅል በሀገሪቱ ላይደርስ ይችል ነበር ሲሉ ገልጸዋል።
ዶ/ር ይልቃል ፤ ጦርነት ከሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ባለፈ ስነልቦናዊ ስብራትን እንደሚያስከትል የአማራ እና ትግራይ ህዝብ በተግባር አይተዋል ያሉ ሲሆን " የአማራ ክልል ህዝብ የትግራይ ህዝብ ወንድሙ እንደሆነ ድሮም አብሮ ይኖር ነበር ወደፊትም ቢሆን አብሮ ለመኖር የተዘጋጀ ህዝብ ነው ፤ ከወንድሙ ጋር የሚያጋጥመውን ችግር በሰላም እና በድርድር ለመፍታት ነው የሚዘጋጀው የሚያስበው። የትግራይ ክልል ከኛ የሚጠይቀው ጉዳይ ካለ በሰላም በውይይት ፣ ከዚያም ባለፈ በህግ መፍታት እንችላለን ይሄን የሰለጠነ መንገድ ሁላችንም ተቀብለን መፈፀም አለብን " ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጦርነቱ የፈጠረውን ቁስል በሚያክም መንገድ መግባባት ፣ መገናኘት እንደ አንድ ሀገር ዜጋ እንደ ወንድም እና እህት ማህበረስብ መተሳሰብ ይገባናል ብለዋል።
" በዚህም ረገድ የአማራ መንግስትም ሆነ የአማራ ህዝብ የትግራይ ህዝብ የኔ ወንድም እና እህት ነው ብሎ የሚያስብ በችግሩ ጊዜ የሚደርስ በመሆኑ በዚያ መንፈስ ነው የምናየው ፤ ሰላም አብሮነትን የሚያፀና ፣ የሚያጠናክር ይሆናል ብለን እምነት እናደርጋለን " ሲሉ አክለዋል።
ከእሥር ፍቺ
መንግሥት ክስ የመሠረተባቸውን የሕወሃት ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ከእስር መፍታቱን የተከሳሾቹ ጠበቃና ቤተሰቦች ገልፀዋል።
ትናንት ከእስር ከተፈቱት መካከል፣ የቀድሞው የትግራይ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አብርሃም ተከስተ፣ አዲስዓለም ባሌማ እና የቀድሞዋ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሂም ይገኙበታል።
ከእስር የተፈቱት ተከሳሾች፣ በደብረጺዮን ገ/ሚካዔልና በጀኔራል ታደሠ ወረደ መዝገብ ስር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩ 16 ሲቪልና 20 ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው።
ተከሳሾቹ የተፈቱት፣ ፍትህ ሚንስቴር በፓርቲው ሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የከፈተውን ክስ ማቋረጡን ተከትሎ ነው።