አሽ ባቲ ካሮሊና ፕሊሽኮቫን በሶስት ዙር ግጥሚያ 6-3 6-7 6-3 በመርታት ለ41 ዓመታት አውስትራሊያ አጥታ የነበረውን የቴኒስ ድል አስመዝግባለች።
የኩዊንስላንዷ ነባር ዜጎች የንጋሪጎዋ ሴት የልጅነት አርአያዋ ሌላዋ የነባር ዜጎች ሴት ኢቮን ጉላጎንግ በ1980 ለአውስትራሊያ ድል ካስገኘች በኋላ የአስውትራሊያ ሴቶች ቴኒስ የመጀመሪያዋ አሸናፊ ሆናለች።

በሌላም በኩል በግብረ አካል ጉዳተኞች የወንዶች ቴኒስ ዲለን አልኮት በዚህ ዓመት ሶስተኛው የሆነውን የዊምብልደን ግራንድ ስላም አሸናፊ ሆኗል።
የሜልበርኑ የግብረ አካል ጉዳተኞች ቴኒስ ኮከብ ለድል የበቃው ዋነኛ ተቀናቃኙን ሳም ሽዶደርን 6-2 6-2 በሆነ ውጤት በመርታት ነው።

ቫይረስ ኒው ሳውዝ ዌይልስ
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ባለፉት 24 ሰዓታት 77 ነዋሪዎቿ በኮሮናቫይረስ መጠቃታቸውንና አንዲት የ90 ዓመት ኣረጋዊት ሕይወት ማለፉን በዛሬው ዕለት አስታወቀች።
ኒው ሳዝ ዌይልስ የቫይረሱን መስፋፋት ለመከላከል የኮሮናቫይረስ ገደቦች ከጣለች ሁለተኛ ሳምንቷን አስቆጥራ ወደ ሶስተኛ ሳምንት ተሸጋግራለች።
ፒሪሚየር ግላዲስ በርጂክሊያን ነገ ሰኞ በቫይረሱ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር ምናልባትም ከ100 በላይ እንደሚያሻቅብ አመላክተዋል።
በአሁኑ ወቅት 15 ፅኑ ህሙማንን፣ አምስት የመተንፈሻ መሣሪያ ተገጥሞላቸው ያሉትን ጨምሮ 52 ሰዎች የሆስፒታል ሕክምና በማግኘት ላይ ናቸው።

