እንደ አውስትራሊያውያን፤ ዕጣ ፈንታችን ሁሌም ባንድ ላይ የተሰናሰለ ነው፡፡
ባለፈው ዓመት ዳግም የጋርዮሽ ዕድሎቻችንን ልብ እንድንላቸው ተደርገናል፡፡ ምን ያህል አንዳችን ያንዳችን ተመርኳዥ እንደሆንን፡፡
በአንድ ዓመት ውስጥ አብላጫው ዓለም በሉላዊ ወረርሽኝ ማነቆ ሳቢያ ትግል ገጥሞት ነበር፡፡ አውስትራሊያውያን ግና በጋራ ድል ለመንሳት በቅተናል፤ የራሳችን በሆነው አውስትራሊያዊ መንገድ፡፡
ለሌሎች ጭምብል ሠርተው ከቸሩቱ የርቀት ትምህርታቸውን እስከተከታተሉቱ ልጆች፤ በአስቸጋሪው የኮቨድ ገደቦች የታወኩት የአረጋውያን መጠለያ ነዋሪዎች፣ እያንዳንዱ አውስትራሊያዊ በክፍለ ዘመን አንዴ ለሚከሰተው ወረርሽኝ ግብረ ምላሽ የየፊናውን ሚና ተጫውቷል።
የአውስትራሊያ ቀን የምልሰታዊ ዕይታ፣ ክብረትና ክብረ በዓል ዕለት ነው።
በአውስትራሊያ ቀን ያን ጉዞ በምልሰት እንቃኛለን፤ ለነፃነታችን የተከፈለውን ዋጋ፣ የታሪካችን ትምህርቶችና ራሳችንን አውስትራሊያውያን ብለን ለመጥራት የቻልንበትን ልዩ ክብረት።
በዛሬዋ ዕለት፤ የነባር ዜጎችን 60,000 ዓመታት ታሪክ እንዘክራለን፤ ጥንካሬያችንንም የነፃ ሰዎች ሉል ከሆነው ዲሞክራሲ እንመዛለን፤ በምድር ላይ በጣሙን ስኬታማ በዝሃባሕል አገር ለሆነችው አገራችንም አድናቆታችንን እንገልጣለን። እኒህ ታሪኮች አንዳቸው ካንዳቸው ጋር አይፎካከሩም፤ አብረው ተዋድደውና ድርና ማግ ሆነው አሉ እንጂ።
እኛ ምንም ዓይነት ተግዳሮቶች ከፊታችን ቢደቀኑም ግብረ ምላሽ የምንሰጥ ጨዋ፣ ፍትሃዊ፣ ሥራ ፈጣሪዎችና ቸር ሰዎች ነን። እንዲሁም፤ ሁሌም የተሻለ ለማድረግ የምንታትር ነን።
በወረርሽኙ ሳቢያ በዚህ ዓመት አከባበራችን ለየት ይላል፤ መፃዒውን ጊዜ የምንመለከተው በተስፋና በይሆናል አመኔታ ነው፤ አንድ ላይ ሆነን መከወን እንችላለን፤ እኒህን አዋኪ ጊዜያትም እንወጣለን በሚል ግንዛቤ።
መልካም የአውስትራሊያ ቀን
ስኮት ሞሪሰን
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር
ጃኑዋሪ 26, 2021