የአውስትራሊያ 650 ሺህ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሌሎች ክርስቲያኖች በዓለ ትንሣኤ ካከበሩ ድፍን አንድ ወር በኋላ ዛሬ እሑድ ሜይ 2 እያከበሩ ነው።
ለበዓሉ አከባበር ልዩነት አስባቡ ሃይማኖታዊው የጁሊያን የዘመን ቀመር ልዩነት ነው።
ከበዓሉ ጋር በተያያዘ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ገደቦች ሳቢያ ቀዝቅዞ የነበረው ገበያ በዚህ ሳምንት ውስጥ ሞቅ ደመቅ ብሎ ሰንብቷል።
የግሪክ ጥፋጭ ሱቆች የክርስቶስን ደም ተምሳሌ ያደረጉ ቀይ ቀለም የተቀቡ ዕንቁላሎችና ሻማዎችን ለኦርቶዶክስ ፋሲካ አቅርበዋል።
የሻማ ጅምላ አቅራቢ ባለቤት ሬና ሙስታካስ በአብዛኛው ሻማዎችን ለልጆች በስጦታ ሲያድሉ እንደነበረና ተምሳሌነቱንም አንስተው ሲገልጡ፤
"ሻማዎቹ የኢየሱስ ብርሃንነትን የሚወክሉ ናቸው። ኢየሱስ በአንደበቱ "እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ" ሲል ነግሮናል። ሻማውን የምሰጠው ልጅም ሲቀበለኝ ያ እንዲሰማው እሻለሁ" ብለዋል።

Ethiopian Christian pilgrims hold candles during an Ethiopian Orthodox ceremony of the "Holy Fire". Source: Getty
የሽብርተኝነት ፍረጃ
የሚንስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 23, 2013 ባካሄደው ስብሰባ “የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” ድርጅቶች በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ መክሮ የውሳኔ ሐሳቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ እንዲቸረው መርቷል።
ይህንኑ አስመልክቶ ይፋ ባደረገው መግለጫው " የበርካታ ዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ እንዲሁም ንብረታቸው ወድሟል፤ ከቀዬአቸውም ተፈናቅለዋል። እነኚህ ጥቃቶች ኅብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው ሥጋት እና ፍርሐት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ፣ ዜጎች እርስ በእርስ እንዳይተማመኑ አድርጓል። እነዚህ ሁሉ የሀገረ መንግሥቱን ህልውና አደጋ ላይ ለመጣል ታቅደው ሲፈጸሙ የነበሩ መሆኑን ከተለያዩ ማስረጃዎች ለመረዳት ተችሏል" በማለት የሁለቱ ድርጅቶች የሁከት ተግባራት ያላቸውን አመላክቷል።
ድርጅቶቹ በሽብር ወንጀል ተግባራት የሚጠየቁባቸውን አንቀጾች ሲጠቅስም፤
- እነኚህ ድርጅቶች ሲፈጸሙና ሲያስፈጽሙ የቆዩዋቸው የጥፋት ተግባራት የሽብር ወንጀል ተግባራት ናቸው። እነዚህ ተግባራት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐወጅ 1176/2012 አንቀጽ 3 ሥር ስለሽብር የወንጀል ድርጊት የተሰጠውን ትርጓሜ ሙሉ ለሙሉ የሚያሟሉ ተግባራት እንደሆኑ በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። እነዚህን የሽብር ተግባራት የፈጽሙ ድርጅቶች አባላትና እና ደጋፊዎቻቸውን እንደ ግለሰብ በተናጠል በሽብር ወንጀል ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ ድርጅቶቹን የሽብርተኛ ድርጅት አድርጎ በመሰየም በሕጉ በተቀመጠው አግባብ የሽብር ወንጀል ድርጊትን በተሻለ ሁኔታ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል ይችላል።
- ስለዚህ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ወሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል።
- እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 23 መሠረት በተመሳሳይ ተግባር በተሰማሩ እና በዚህ ውሳኔ ሐሳብ መሠረት ከተሰየሙት የሽብርተኛ ድርጅቶች ጋር ትብብር፤ ትሥሥር ወይም የሐሳብ እና የተግባር ዝምድና ያላቸው ድርጅቶችና ግለሰቦች ላይም ይህ ውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚ ይሆናል
ብሏል።
ምርጫ ታዝማኒያ
የታዝማኒያ የታችኛው ምክር ቤት ካሉት 25 ወንበሮች ውስጥ 13ቱን በማሸነፍ አብላጫ ወንበሮች ያሉት መንግሥት ለማቆም የሚያስችለው የድምጽ ቆጠራ ዛሬ ሜይ 2 በመከሄድ ላይ ይገኛል።
የሌበር መሪ ሬቤካ ዋይት ድል መነሳታቸውን አምነው በመቀበል ተቀናቃኛቸውን የሊብራል መሪ ፒተር ገትዊንን "እንኳን ደስ ያለዎት" ብለዋል።
ወ/ሮ ዋይት ምንም እንኳ ሌበር በአሁኑ ምርጫ ማሸነፍ ቢሳነውም ታዝማኒያን ለማሻሻል በርትቶ እንደሚሠራ ገልጠዋል።

Labor leader Rebecca White said the party will continue to advocate on policies to improve infrastructure and health services. Source: SBS News/Sarah Maunder
ፕሪሚየር ፒተር ገትዊን በበኩላቸው ዳግም ታዝማኒያን የመመራት ዕድል በማግኘታቸው ከፍ ያለ ክብር የተሰማቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ ዛሬ ቀጥሎ የሚውለው የድምፅ ቆጠራ ሲጠናቀቅም ራሳቸውን ችለው መንግሥት ማቆም የሚያስችላቸውን 13ኛ ወንበር እንደሚያገኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።

Peter Gutwein has been re-elected as Premier of Tasmania. Source: Getty
እስከ ዛሬ እሑድ ማለዳ ድረስ ሊብራል 12 ሌበር 8 ግሪንስ 2 የምክር ቤት ወንበሮችን አሸንፈዋል።