"የአማራ ክልል ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም 2 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ያስፈልጋል" አምባሳደር አባቢ ደምሴ

*** የአማራ ክልል ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም ከ46 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላርስ በላይ በአውስትራሊያውያን - ኢትዮጵያውያን ተለገሰ

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

በአማራ ክልል ተፈናቅለው ያሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ያስችል ዘንድ 2 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር እንደሚያስፈልግ አምባሳደር አባቢ ደምሴ ገለጡ።

አምባሳደር አባቢ ይህን የገለጡት ጁላይ 11 በተለይም ከሰሜን ሸዋ አስተዳደርና ከኦሮሚያ አስተዳደር ዞን የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው ለመመለስና ለማቋቋም፤ እንዲሁም በጥቃቱ የወደሙ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትንና የመሠረተ ልማት አውታሮችን መልሶ ለማቋቋም የገንዘብ ልገሳ ለማሰባሰብ እንዲያስችል በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው በይነ መረብ መድረክ ነው።

አምባሳደሩ በአጣየ ብቻ 1,529 መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን፣ 3,965 የቤተሰብ መሪዎች በተለያዩ ቦታዎች የነፍስ አድን እርዳታ ብቻ እየተደረገላቸው እንደሚገኙ፣ 1,281 አረጋውያን፣ 1,847 አካል ጉዳተኞች፣ 117 ወላጆቻቸውን ያጡ ሕፃናት እርዳታ እንደሚሹና 504 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አመላክተዋል።
Ambassador Ababi Demissie.
Ambassador Ababi Demissie. Source: SBS Amharic


አምባሳደር አባቢ አክለውም፤

  • በአጣየ አምስት ወረዳዎች ሰባት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል
  • በአራት ወረዳዎች አራት የጤና ጣቢያዎች ወድመዋል
  • በሶስት አካባቢዎች 23,250 ሰዎች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ ስድስት የጉድጓድ ውኃዎች ለኅብረተሰቡ ጥቅም እንዳይሰጡ ሆነዋል
  • 11 ሆቴሎች ተቃጥለዋል
  • 49 የእህል መጋዘኖች
  • 350 ሱቆች እንደወደሙና
  • 12 የእምነት ተቋማት (ቤተክርስቲያናትና ቤተ መስጊዶች) ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጠዋል።
ቀደም ሲልም ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ባደረጉት ንግግር "በክልላችን ከልዩ ልዩ ሥፍራዎች ከ800 ሺህ በላይ ተፈናቅለው ይገኛሉ፤ ከ300 ሺህ በላይ ወገኖቻችን ያለመጠለያ ቀርተዋል" ያሉ ሲሆን፤ አክለውም "ኢትዮጵያውያን በተገፉ ቁጥር እንደምስማር እየጠነከሩ ይሄዳሉ። ወገኖቻችን በሚቀጥለው ዓመት በመጠለያዎች እንዳይቀሩ" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
Dr Fanta Mandefro.
Dr Fanta Mandefro. Source: SBS Amharic
አምባሳደር አባቢ የሚሰበሰበው ገቢ፤

  • ተፈናቃዮች ከተበተኑበት አካባቢ በቀዬአቸው መጠለያ እንዲያገኙ
  • ቋሚ የሆነ መጠለያ እንዲኖራቸውና
  • በማኅበረሰቡ ላይ የደረሰውን የሥነ ልቦና ስብራት መጠገኛ እንደሚውል አስታውቀዋል።
በዕለቱ በችሮታ ማሰባሰቢያው ላይ ከተሰበሰቡት ታዳሚዎች በጥቅሉ ከ46 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላርስ በላይ መለገሱን የዕለቱን ገቢ ማሰባሰቢያ ሰብሳቢ አቶ በሪሁን ደጉ - በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሙሉ ሥልጣን ሚኒስትርና ምክትል ሚሽን መሪ ገልጠዋል።  

ቀደም ሲልም በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ወገኖች ለመፈናቀል የተዳረጉባቸውን ሁኔታዎችና የዕለቱም የገቢ ማሰባሰብ ተግባር የወገኖችን ሕይወት ለመታደግ በእጅጉ ከፍ ያለ ሰብዓዊ ችሮታ መሆኑን ለታዳሚዎች አሳስበዋል።
Ambassador Dr Muktar Kedir.
Ambassador Dr Muktar Kedir. Source: SBS Amharic


ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያውያን - አውስትራሊያውያን ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፣ ለመከላከያ ሠራዊት ድጋፍ፣ ለሕዳሴ ግድብ ያበረከቷቸውን በመቶ ሺህ ዶላርስ የሚቆጠሩ አስተዋፅዖዎችን አንስተው "ታሪክ የማይረሳው አኩሪ አስተዋፅዖ" በማለት ምስጋናቸውንና የልገሳ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።     

   


Share

Published

By Kassahun Seboqa Negewo

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
"የአማራ ክልል ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም 2 ቢሊየን የኢትዮጵያ ብር ያስፈልጋል" አምባሳደር አባቢ ደምሴ | SBS Amharic