በአውስትራሊያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ "ኢትዮጵያን እናድን" ፋይናንስ አባላት ዛሬ ሴፕቴምበር 25 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያዩ።
ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያን እናድን አስተባባሪ አቶ አያሌው ሁንዳሳ የዕለቱን አጀንዳ አስተዋውቀዋል።
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ናቸው።
አምባሳደሩ በንግግራቸው "ኢትዮጵያ የልጆቿን ድጋፍ ከምንም በላይ በምትፈልግበት ወቅት ወደ ግብር የለወጣችሁ የ Save Ethiopia አባላትን በራሴና በሚሲዮኑ ስም አመሰግናለሁ። Save Ethiopia ወቅታዊና ትክክለኛ platform ነው" ብለዋል።
ከአምባሳደሩ ንግግር በመቀጠል አቶ ለማ ዋቀዮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳያስፖራ ተሳትፎና ቢዝነስ ሥራ አስፈፃሚ የውጭ ምንዛሪ ምንጮችንና የኢትዮጵያን እናድንን ጥረት አስመልክተው ተናግረዋል።

Ambassador Dr Muktar Kedir. Source: SBS Amharic
የኢትዮጵያ ምንዛሬ ምንጮች ውስን መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዋነኛነት የውጭ ብድር፣ እርዳታ፣ የውጭ አቅርቦትና ሃዋላ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የውጭ ብድርና እርዳታ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የውጭ አቅርቦት ገቢ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት የሚጠይቀውን ያህል አለመሆኑን ገልጠዋል።
አያይዘውም "የኢትዮጵያን እናድን ተነሳሽነት ትክክለኛም ወቅታዊም ነው። የውጭ ምንዛሬ ክፍተቱን ለመድፈንም ያስችላል። ካላችሁበት አገር ሆናችሁ ያላችሁን ገንዘብ እዚህ [ኢትዮጵያ] ማስቀመጥ ትችላላችሁ። ልዩነቱ አድርሻ መለወጥ ብቻ ነው። ይህን ማድረግ አገርን ማገዝ ነው። የጥቁር ገበያው ከምጣኔ ሃብት ጉዳት አልፎ የሰው ሕይወትን ጭምር እያጠፋ ነው" ብለዋል።

Lemma Waqeyo. Source: SBS Amharic
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሃዋላ ክፍል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ሊቁ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውጭ ካሉ 60 በላይ ባንኮች ጋር ገንዘብ ከአገር ውስጥ ወደ ውጭ፤ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ በማሸጋገር ላይ ይገኛል። ውጭ ያለው ገንዘብ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ተቀመጠ ማለት ከ80 ፐርሰንት ለመንግሥት (የመንገድና ቴሌኮም አገልግሎቶች፣ የውጭ አገር መምህራን ደመወዝ ለመሳሰሉት) 20 ፐርሰንት ለግል ፕሮጄክቶች ይውላል" ሲሉ ተናግረዋል።
በውጭ አገር ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቁጠባና የቤት ግዢና ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ የባንክ ሂሳቦችን የመክፈትና የወለድ ጥቅሞችንንም የሚያስገኙ ግልጋሎቶችን እንደሚሰጥ አብራርተዋል።

Yohannes Liku. Source: SBS Amharic
በአጀንዳው መሠረትም ዶ/ር ከፋለ መኮንንና አቶ ግርማ ፈይሳ የኢትዮጵያን እናድን ተነሳሽነት ዓላማ፣ እስካሁን የተደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ ታሪካዊና ወቅታዊ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና እርዳታን አስመልክተው ለታዳሚዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።