ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የነበሯት ሕገ መንግሥታት የረቀቁትና የጸደቁት በተከታታይ የወቅቱ የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት የነበሩ መሪዎች አስቀድመው ባስቀመጡት መሥፈርት መሠረት በመለመሏቸው ግለ ሰቦችና ቡድኖች ተሳትፎ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕገ መንግሥቶቹን በማርቀቅና በማጽደቅ ሂደት ውስጥ ተሳትፎ አልነበረውም ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ አገራችን በሕዝብ የተመረጠና ለሕዝብ የሚሠራ መንግሥት ኖሯት አያውቅም ማለት ነው።
ለምን አልነበራትም ብሎ ለመመራመር ራሱን የቻለ ጥልቅ ማኅበረ ሰባዊ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ አጭር ጽሁፍ የሚዳሰስ አይደለም ለማለት ነው።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን ለሰፈነው ፖሊቲካዊ፣ ማኅበረ ሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ የ1995ቱ ሕገ መንግሥቱ ወሳኝ አሉታዊ ሚና አለው ተብሎ ስለሚገመት፣ አንዳንድ ምሁራንና የፖሊቲካ ኤሊቶች የሚያነሷቸውን የቅሬታ ነጥቦች አንስቼ ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ የራሴን አስተያየት በመሠንዘር፣ ሌሎች በመስኩ ልምድና ዕውቀት ያላቸው ባለ ድርሻ አካላት ደግሞ ሃሳባቸውን በማካፈል ጤናማ ውይይት እንድናደርግ ከወዲሁ ለመጋበዝ እፈልጋለሁ።
የዚህ ጽሁፌ ዋነኛው ዓላማ ይኸው ነው።
አንድ ሕገ መንግሥት የአገሩ ሕጎቹ ሁሉ እናት የሆነውን ያህል፣ እንደ አስፈላጊነቱ ደግሞ ለማኅበረ ሰቡ ዕድገትና የሕዝቦች ፍላጎት ተመጣጣኝ እንዲሆን ከማለት በየጊዜው ለመሻሻል ይዳረጋል።
እንደ ቅዱሳን መጻሕፍት አይነኬ አይተኬ ስላልሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ደግሞ መሻሻል ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹ ተፍቆ በሌላ አዲስ ሕገ መንግሥት ሊተካ ይችላል።
ሕገ መንግሥታት ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተቀረጹና የጸደቁ ከሆነ ዲሞክራሲያዊ የመሻሻል ቅድመ ሁኔታዎች እዚያው ሕገ መንግሥት ውስጥ ተካትተው ይገኛሉ።
በአንጻሩ ደግሞ፣ ኢዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ማለትም በአብዮታዊ ትግል ስኬት ሕገ መንግሥት ሊሻሻል ወይም ሊፋቅ ይቻላል። ለምሳሌ የወታደራዊው ደርግና የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥታት በአብዮታዊ ትግል ስኬት የተፋቁ ነበሩ። እንደዚያም ሆኖ ግን፣ አሁን በተግባር ውሎ የምንጠቀምበት የ1995ቱ ሕገ መንግሥት የአብዮታዊ (ዓመጽ) ትግል ውጤት ቢሆንም፣ እሱን ለማሻሻል ወይም ለመፋቅ የሚያስችሉ ዲሞክራሲያዊ ቅደም ሁኔታዎችን ግን በውስጡ አካትቷል። አንቀጽ 105 ልብ ይሏል።
የ1995ቱን ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ ሶስት ተቃራኒ ሃሳቦች እየተስተናገዱ ነው።
አንደኛው ወገን፣ ሕገ መንግሥቱ የግልንም ሆነ የብሔር / ብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጠ ስለሆነ በምንም መልኩ መነካት የለበትም ይላል።
ሁለተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የግልና የቡድን መብት በሙሉ ያረጋገጠ ቢሆንም፣ አፈጻጸም ላይ ችግር ስላለ አንዳንድ አንቀጾቹ መሻሻል አለበት ይላል።
ሶስተኛው ቡድን ደግሞ፣ ሕገ መንግሥቱ ከጽንሱ ጀምሮ እስከ ማጽደቁ ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሕዝብ ያልተሳተፈበት፣ የማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሶቻችን አልፋና ዖሜጋ ስለሆነ ተፍቆ በአዲስ ሕገ መንግሥት መተካት አለበት ይላል።
ሶስቱም የየራሳቸው የሆነ አሳማኝ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል። ግን ሃሳቦቹ በግልጽ ለሕዝብ ቀርበው ባለ ድርሻ አካላት ሃሳብን በሃሳብ የሚሞግቱበትና የሚወያዩበት መድረክ ስለሌለ፣ ይኸኛው ሃሳብ ከዚያኛው የተሻለ ነውና እንቀበለው የምንልበት ደረጃ ላይ አይደለንም።
ስለዚህ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ግለ ሰቦችና ቡድኖች ከሁሉ በፊት ይህን ነጻ ውይይት የምናካሄድበትን መድረክ መፍጠር ተቀዳሚ የቤት ሥራቸው መሆን አለበት ባይ ነኝ።
እስከዚያ ድረስ ደግሞ፣ ምንም እንኳ የውጭ አገር ዜጋ ብሆንም፣ እንደ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሕግ ባለ ሙያ፣ ጉዳዩ በተዘዋዋሪ ስለሚመለከተኝ፣ ይህንን ለውይይት መነሻ ይረዳል ብዬ የማምንበትን ጽሁፍ ላካፍላችሁ ወሰንኩ።
በግሌ በአቋም ደረጃ፣ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል አለበት ከሚሉ ወገን ነኝ።
በዚህኛው ጽሁፌ የማተኩረው ግን፣ መሻሻል አለባቸው በምላቸው አንቀጾች ላይ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱ መፋቅ አለበት የሚሉትን ቡድኖችን አንዳንድ ሃሳቦችን ለመሞገት ነው።
የ1995 ዓ/ም የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት
በ1995 ዓ/ም የጸደቀው የፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በይዘቱ ሆነ በቅርጹ ከፊተኞቹ ያገራችን ሕገ መንግሥታት ሁሉ የተለየ መሆኑን ብዙዎቻችን እንገነዘባለን። በተለይም የግለ ሰቦችንና የቡድን መብቶችን በማያሻማ መልክ በማካተቱ! ግን ደግሞ፣ ልክ እንደ ፊተኞቹ ሕገ መንግሥታት፣ አርቃቂዎቹንና አጽዳቂዎቹን ከማኅበረ ሰቡ መሃል መልምሎ ያዋቀረው በጊዜው የፖሊቲካ ሥልጣኑን የጨበጠው ወያኔ መራሹ የኢሕአዴግ መንግሥት ነበር።
ኢሕአዴግ የሥልጣን መንበሩን አረጋግቶ የሽግግር መንግሥት ካቋቋመ በኋላ ሕገ መንግሥቱንም እንደሚመቸው አስረቅቆ ማጽደቁ ከነጻ አውጪ ብሔርተኛ ድርጅቶች የሚጠበቅ ነበር።
ሕወሓት ነፍጥ አንግቶ ለዓመታት በየዱሩ ማዕከላዊውን መንግሥት ሲታገል የነበረው ይህንኑ የብሔር ነጻነት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ስለ ነበር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አንቀጽ 39ን የመሰለ ሥር ነቀል የሕዝቦችን መብት ማረጋገጫ ማካተቱ የሚጠበቅ ነበር።
አራት ኪሎ ደርሶ ፌዴራል ኢትዮጵያን የመገንባት ሃሳብ እስኪመጣለት ድረስም፣ እወክለዋለሁ ብሎ ያወጀውን ሕዝብ “ነፃ ለማውጣት” ይተጋ ስለ ነበር የሚያጸድቀው ሕገ መንግሥት ዋነኛ ትኩረቱ የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ያነሰ ይዘት ይኖረዋል ብሎ መገመት የፖሊቲካ መኃይም መሆን ይመስለኛል።
ሕገ መንግሥቱ ይፍረስ የሚሉ ቡድኖች ከሚያነሷቸው ነጥቦች አንዳንዶቹ፣
ሀ) “ሕገ መንግሥቱ የአገሪቷን አስተዳደራዊ መዋቅር በክልል ሲከፋፍል፣ ሕዝቦች በብሔር እንዲከፋፈሉና እርስ በእርስ እንዲጣሉ አድርጎ አገሪቷን ከዳር እስከ ዳር በእርስ በርስ ግጭት እያናወጣት ይገኛል” ይላሉ ተቃዋሚዎቹ።
ዛሬ በየክልሎቹ እየተከሰተ ያለውን የእርስ በርስ ግጭት ዕውን ሆኖ ስናስተውል፣ አባባሉ የሆነ ዓይነት እውነትነት አለው። ሆኖም ግን የግጭቶቹ መንሥዔ ፌደራላዊ ሥርዓቱና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው ብሔርና ቋንቋ ተኮር የክልል አወቃቀር ፖሊሲ ነው ወይ ብለን ብንጠይቅ፣ መልሱ ሌላ ሆኖ እናገኘዋለን።
ሕገ መንግሥቱ በትክክል ያስቀመጠው ክልሎች የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች ብቻ ሃብት አለመሆኑን ነው። የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በግልጽ አማርኛ፣ የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች የክልሉ የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል እንጂ የክልሉ ባለቤት ናቸው አይልም። የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት መሆን ማለት ደግሞ ከክልሉ ብሔር ተወላጆችና በክልሉ በሕጋዊነት ከሚኖሩ በስተቀር የሌላ ክልል ብሔር ተወላጆች በክልሉ የፖሊቲካና የኤኮኖሚ ሕይወት ተጠቃሚ ሊሆኑ አይችሉም ማለት አይደለም። ከታች እመለስበታለሁ።
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በግልጽ አማርኛ፣ የክልሉ ተወላጅ ብሔሮች የክልሉ የፖሊቲካ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ይላል እንጂ የክልሉ ባለቤት ናቸው አይልም።ባይሳ ዋቅ-ወያ
ለ) “ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል ባለቤትነት ለራሳቸው ብሔር ተወላጆች ብቻ አድርገው ከመቁጠራቸው የተነሳ የሌሎች ክልል ብሔር ተወላጆች እንደ ልባቸው እንዳይዘዋወሩና ኑሮአቸውን እንዳይመሠርቱ አድርጓል” ይላሉ።
ሕገ መንግሥቱ ግን የሚለው ሌላ ነው።
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32(1) በግልጽ እንዳስቀመጠው፣ እንኳን የኢትዮጵያ ዜጋ ይቅርና የውጭ አገር ዜጎች እንኳ ሳይቀሩ በማንኛውም የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ ለመዘዋወር ወይም ለመኖር እንደሚችሉ ሲያረጋግጥ፣
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጪ ዜጋ በመረጠው የሃገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመመሥረት ነጻነት አለው” ይላል።
የኦሮምያ ክልላዊ ሕገ መንግሥት 34(1) ለምሳሌ፣
“ኢትዮጵያውያን የሆኑ የሌሎች ክልሎች ተወላጆች በዚህ ክልል ውስጥ እንደ ማንኛውም የዚህ ክልል ተወላጅ ሠርቶ የመኖር፣ ከሥፍራ ሥፍራ በነጻ የመዘዋወር፣ ሃብትና ንብረት የማትረፍና የመያዝ መብት አላቸው” ይልና፣
በአንቀጽ 34(2) ሥር ደግሞ፤
የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (የክልሉ ብሔር ተወላጅ ያልሆነ ማለት ነው) በማንኛውም የክልሉ መንግሥታዊ ሥራ ውስጥ ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው” ብሎ ይደነግጋል።
የአማራ ክልላዊ ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ መልኩ በአንቀጽ 32 ሥር እንዳስቀመጠው፣
“ማንኛውም የክልሉ ነዋሪ ወይም በሕጋዊ መንገድ በክልሉ ውስጥ የሚገኝ ሰው በመረጠው የክልሉ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቤት የመሥራት፣ ሠርቶ የመኖር፣ ሃብት የማፍራትና የመያዝ እንዲሁም በፈለገ ጊዜ ከክልሉ የመውጣት መብት አለው” ይልና፣
በአንቀጽ 33 ሥር ደግሞ፣ “የክልሉን የሥራ ቋንቋ የሚያውቅ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በማንኛውም የክልሉ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ሥራዎች ተመርጦ ወይም ተመድቦ የመሥራት መብት አለው” ይላል።
ሐ) ሌላው የሕገ መንግሥቱ ተቃዋሚዎች ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ፣ በሌሎች አገራት እምብዛም ያልተለመደውን የአንድን ብሔር ተገንጥሎ የራሱን አገር እንዲመሠርት የሚገፋፋ አንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ ነው።
በኔ ግምት፣ አንቀጽ 39 የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንዳቸው ሌላውን ሳይጨቁኑ በእኩልነት እንዲኖሩና፣ አንደኛው ግን “በሌላኛው ብሔር ተጨቁኜያለሁ፣ መብቴ ተጥሷል፣ አብሬ በእኩልነት ለመኖር የሚያስችለኝ ዕድል ተሟጥጦ አልቆአል” ካለ የመገንጠል መብቱ እንደሚጠበቀለት ዋስትና እንዳለው ለማስረገጥ እንጂ አገር እንድትከፋፈል ተብሎ የተካተተ አይደለም።
በታኅሳስ 1992 ዓ/ም በጸደቀው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ለምሳሌ፣ ለአንድ ትዳር መፋታት ሁለቱም ወገኖች በእኩል ደረጃ የፍቺ ጥያቄ ለፍርድ ቤት ለማቅረብ የመቻል መብት የሚያረጋግጡ አንቀጽ 76 እና 81(1) መካተታቸው “መብቴ ተጥሶብኛል፣ ተፋትቼ የራሴን የወደ ፊት ዕድል ራሴ እወስናለሁ” ብሎ ለመወሰን ሴቲቷም ከወንድ እኩል የፍቺ ጥያቄ ለማቅረብ ለመቻሏ ዋስትና ለመስጠትና ባልየው ሚስቲቱ ከሱ ተፋትታ የራሷን ዕድል በራሷ የመወሰን መብት እንዳላት አውቆ መብቷን ከመጣስ እንዲቆጠብ ታስቦ እንጂ የኢትዮጵያውያንን ትዳር ለማፈራረስ አይደለም።
በዚያው ልክ፣ ከታሪክ እንደምንረዳው፣ አንድ ብሔር ተገንጥሎ የራሱን ግዛት ለመፍጠር ከፈለገ በግድ የሕገ መንግሥቱን መሥፈርት ማሟላት አይጠበቅበትም። ሕገ መንግሥቱን በጉልበትም ጥሶ የራሱን አገር መመሥረት ይችላልና።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የራሷን ነጻ አገር የመሠረተችው የሕገ መንግሥቱን መሥፈርት አሟልታና አንቀጽ 39ን ተጠቅማ ሳይሆን በራሷ ወታደራዊ ጥንካሬ ብቻ ነው። ስለዚህ የአንቀጽ 39 በሕገ መንግሥቱ ውስጥ መካተቱ ዛሬ በማንነት ላይ በተመሠረቱ አለመግባባቶች እየተከሰተ ላለው የእርስ በርስ ግጭቶች አንዳችም አስተዋጽዖ አላበረከተም ባይ ነኝ።
ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀበት ጊዜ ጀምሮ ማለትም ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ውስጥ ለምሳሌ አንቀጽ 39ን ጠቅሶ ለመገንጠል ጥያቄ ያቀረበ አንድም የኢትዮጵያ ብሔር ወይም ክልል የለም።
በየጊዜው የተነሱ ተቃዋሚ ቡድኖችም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው እንጂ አንዳቸውም የመገንጠልን ጥያቄ አላቀረቡም። ለምሳሌ፣ ቄሮዎች አንድም ጥይት ሳይተኩሱ የተሰካ ሰላማዊ ትግል አካሄደው ሕወሃት ወራሹን መንግሥት ሲገረስሡ “ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይጠበቅ” “የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በተመረጡ ሕጋዊ ተውካዮቹ ይተዳደር” ነበር እንጂ ያሉት፣ በትግሉ ሂደት ውስጥ 5000 ወጣቶች ተሠውተባቸውም፣ አንድም ቦታ ላይ የመገንጠል ጥያቄ ኣላነሱም።
ዛሬም የትጥቅ ትግል እያካሄደ ያለው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ በፌዴራል ኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ሁለቴ ለድርድር ሲቀመጥ፣ ዓላማው ሕገ መንግሥታዊ መብትን ለማስከበር እንጂ ለመገንጠል አይደለም።
ኦነግም ከ1991 ወዲህ አንድም ጊዜ የመገንጠል ጥያቄ አላነሳም፣ በሕገ መንግሥቱም መሠረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦና ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ ዛሬም በሰላማዊ መንገድ እየታገለ ይገኛል።
ፋኖም “የአማራ ሕዝብ ለጥቃት ተዳርጓል” እና ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ይከበርለት ነው እንጂ የሚለው፣ የአማራ ሕዝብ/ክልል ከኢትዮጵያ ተገንጥሎ የአማራን ሬፑብሊክ ይመሠርት ብሎ አንድም ቦታ ላይ የመገንጠል ጥያቄን ሲያነሳ አልተስተዋልም።
ሕወሓትም ወደ ነበርኩበት የፖሊቲካ ሥልጣን ከፍታ ልመለስ ብሎ ከመንግሥት ጋር ተጋጨ እንጂ የመገንጠልን ጥያቄ አላነሳም።
ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ኦነግና ሕወሓት በ1991 ዓ/ም የደርግ መንግሥትን ገርስሠው የፖሊቲካ ሥልጣን ሲረከቡ፣ ፍላጎቱ ቢኖራቸው ኖሮ እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ይዘው ከኢትዮጵያ ተገንጥለው የየራሳቸውን ነጻ አገር ከመመሥረት የሚያግዳቸው አንዳችም ምድራዊ ኃይል አልነበረም። ግን አላደረጉም።
መ) ሕገ መንግሥቱ፣ ከጥንስሱ ጀምሮ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረና ያንን ብሔር/ሕዝብ ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀና ሂደቱ ሁሉንም አካታች ስላልሆነ፣ መፍረስ አለበት ይላሉ ተቃዋሚዎቹ።
በዚህ ጉዳይ ላይ፣ ከጥቂት መኃይም ኤሊቶች፣ ከዩቲዩብና ቲክቶክ አደዳቢ ክርክርና ጽሁፍ ሌላ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ አንዳችም ማረጋገጫ የለም።
ከሕገ መንግሥቱ 107 አንቀጾች ውስጥ አንድም ቦታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አንድን ብሔር በስም ጠርቶ ዛሬም ሆነ ጥንት ለተከሰተው ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ ተጠያቂ ያደረገበት አንቀጽ የለም።
በቅንነት አባባሌን በውል ለመረዳት በጉዳይ እየተቆረቆሩ ያሉ ባለ ድርሻ አካላት ሕገ መንግሥቱን እንዲያነቡ እየጠየቅሁ፣ በደፈናው ግን፣ የሕገ መንግሥቱን ቃልና መንፈስ ለመረዳት የሕገ መንግሥቱን መግቢያ እንደሚከተለው ጠቅሼ አስቀምጫለሁና አንድም ቦታ ላይ ቃሉም ሆነ መንፈሱ በአንድ ብሔር ላይ አለማነጣጠሩን አንብባችሁ እንድትረዱ እጠይቃለሁ።
የሕገ መንግሥቱ መግቢያ (preamble)እንዲህ ይላል፣
እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች፣
“በሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ኤኮኖሚያዊና ማኅበረ ሰባዊ እድገታችን እንዲፋጠን የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን በነጻ ፍላጎታችን፣ የሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖሊቲካ ማኅበረ ሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፣
ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰባዊ መሠረታዊ መብቶች መከበራቸው፣ የጾታ እኩልነት መረጋገጡ፣ ባሕሎችና ኃይማኖቶች ካለ አንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፣
ኢትዮጵያ አገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፣ የየራሳችን መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበረንና ያለን፣ ብሔር ብሔረ ሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረን አብረን የኖርንባትና የምንኖርበት አገር በመሆንዋ፣ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፣
መጪው የጋር ዕድላችን መመሥረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፣
ጥቅማችንን መብታችንና ነጻነታችንን በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኤኮኖሚ ማኅበረ ሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን…….. ይህንን ሕገ መንግሥት አጽድቀናል ይላል። (ሥርዝ የኔ)
በሕገ መንግሥቱ መግቢያ የተካተተው “ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት” የሚለው አባባል፣ ሕገ መንግሥቱ በአንድ ብሔር ላይ አነጣጣሮአል ለሚሉ ወገኖች እንደ ማሳመኛ ሰበብ እንደሚቀርብ ብዙ ጊዜ ይስተዋላል።
በኢትዮጵያ ሕዝቦች መካከል የነበረው ግንኙነት ደግሞ በርግጥም የተዛባ መሆኑን ደግሞ ቀደም ብዬ ያቀረብኳቸው አሳማኝ ታሪካዊ ማስረጃዎች ስለነበሩ፣ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ግንኙነቱ የተዛባ መሆኑን መግለጹ በአንድ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው ማለት ሆን ብሎ ለሆነ የፖሊቲካ ግብን ለማሳካት ከማለት ሕዝቦችን ለማወናበድ ጽንፈኛ ኤሊቶች በየጎጣቸው የፈበረኩት ርካሽ ሸቀጥ ይመስለኛል።
በኔ ግምት እንኳን ያኔ፣ ዛሬም ቢሆን ከሕገ መንግሥቱ ቃላትና መንፈስ ውጭ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግንኙነት ያልተዛባ ነው ብሎ ለመናገር የሚቻል አይመስለኝም።
ሠ) “ሕገ መንግሥቱ ሲቀረጽም ሆነ ሲጸድቅ የኔ ብሔር ተወካዮች አልተካፈሉበትም፣ ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ በኛ ብሔር ዘንድ ተቀባይነት የለውምና እንዳለ ተሠርዞ አዲስ ሕገ መንግሥት ይቀረጽ” ይላሉ የአንዳንድ ብሔር ኤሊቶች።
ቅሬታቸው በተወሰነ መልኩ እውነትነት አለው። ግን ደግሞ፣ የሕገ መንግሥቱን ቀረጻና ማጽደቅ ሂደትን የመራው የኢሕአዴግ መንግሥት ራሱ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ያልተመረጠና ማንንም የማይወክል ስለሆነ፣ ሕገ መንግሥቱን ለማርቀቅና ለማስጸደቅ የመለመላቸው ግለ ሰቦች በሕዝብ የተመረጡ መሆን ነበረባቸው ብሎ መከራከር ደግሞ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ የመጠበቅ ያህል ነው።
በያኔው ሂሳብ፤ ወያኔ መራሹ መንግሥት፣ ልክ እንደ ፊተኞቹ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ አስቀድሞ ባስቀመጠው መሥፈርት መሠረት ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተወካዮችን ራሱ መርጦ አዲስ አበባ ድረስ አስመጥቶ በማርቀቁና በማጸደቁ ላይ አሳትፏቸዋል።
ከታሪክ ሰነድ የምንረዳው፣ የአመራረጥ ሂደቱ ግልጽ አልነበረም እንጂ፣ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ/ም ሕገ መንግሥቱን በማጽደቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ለምሳሌ የአማራ ክልል (ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃም እና ሰሜን ሸዋ) በ182 ሰዎች ሲወከል፣ ከተካፋዮቹ አንዱ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አለነ የደላንታን የምርጫ ወረዳ ወክለው በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል።
ስለሆነም፣ ሕገ መንግሥቱ የረቀቀውና የጸደቀው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ራሳቸው በወከሏቸው ግለ ሰቦች ሳይሆን ኢሕአዴግ በራሱ መሥፈርት መሠረት በመረጣቸው መጽደቁ ነው እንጂ ሕገ መንግሥቱን በማርቀቅና በማጽደቅ ሂደት ውስጥ ያልተካፈለ የኢትዮጵያ ሕዝብ/ብሔር ነበረ ብሎ መከራከር በማስረጃ የተደገፈ አይመስለኝም።
መደምደምያ
ስለዚህ ዛሬ በአንዳንድ ክልሎች እየተከሰተ ያለው ማንነትን መሠረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭትና ብሎም መገዳደል፣ አልፋና ዖሜጋ ምክንያቱ የፌዴራል አወቃቀሩ በክልል በመደረጉ ሳይሆን፣ የሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ በትክክል ሥራ ላይ ባለመዋሉ ነው ባይ ነኝ።
የሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ ቢከበርና በትክክል ቢተገበር ኖሮ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሁሉም ክልሎች በነጻ የመዘዋወርና የመኖር መብት አለውና።
ስለዚህ መኮነን ያለብን ሕገ መንግሥቱን ሳይሆን ሕገ መንግሥቱን በትክክል መተግበር ያልቻለውን ወይም ያልፈለገውን መንግሥትንና ተጓዳኝ ተቋማትን ብቻ መሆን አለበት።
በፍጥረት ለምናምን ሰዎች፣ በማኅበረ ሰብ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያዎቹ የመተዳደርያ ደንቦች ለምሳሌ አሥርቱን የአምላካችን ትዕዛዛት፣ ዛሬ ብዙ የክርስትና እምነት ተከታዮች በትክክል ሲተገበር አይስተዋልም።
ሥርቆት፣ ግድያ፣ ማመንዘር ገሃነም የሚያስገቡ ኃጢያት መሆናቸው እየተነገራቸው፣ በምድራችን ላይ፣ ኢትዮጵያውያንንም ጨምሮ የሰው ልጆች ዛሬም ይሠርቃሉ፣ ይገድላሉ፣ ያመነዝራሉ ወዘተ።
ስለዚህ፣ የሰው ልጆች ሕግጋቱን ጥሰው ስለሚጋደሉና ስለሚሠርቁ ብቻ፣ አሥርቱ ትዕዛዛትን ያቀፈው መጽሃፍ ቅዱስም ፈርሶ ትዕዛዛቱም በሌሎች ሕግጋት ይተኩ ማለት ሕገ ወጥ መሆናችንን ያሳይ እንደው እንጂ ጉድለቱ አሥርቱን ትዕዛዛት ካቀፈው ከመጽሃፍ ቅዱሱ ነው ብሎ መደምደም ትክክል አይደለም።
አሥርቱ ትዕዛዛት በሰው ልጆች ተጥሰው ሰዎች ቢገዳድሉ፣ ቢሠራረቁና አመንዝራነት ቢስፋፋ መለወጥ ያለበት የሰው ልጆች ጠባይና ግንዛቤ ነው እንጂ መጽሓፍ ቅዱሱ መሆን የለበትም።
መሆን ያለበትና ትክክለኛው አካሄድ፣ የሰው ልጆች ሕግጋቱን ጥሰው ገሃነም እንዳይገቡ ባለ ድርሻ አካላት አንዳች ዓይነት ማሕበረ ሰባዊ መርሃ ግብር ቀርጸው ሕዝቡ መለኮታዊ ትዕዛዛትን አክብሮ ወደ ገነት እንዲገባ ይደረጋል እንጂ፣ መጽሃፍ ቅዱስን ኮንኖ ሌላ መጽሃፍ ቅዱስ እንዲጻፍ መወትወት የለበትም ባይ ነኝ።
ሕገ መንግሥት መለኮታዊ ሰነድ አይደለም ብለናል። ስለዚህ በማንኛውም ጊዜ በሕዝቡ ፍላጎት መሠረት ከላይላይና ታይታይ መዋቅሩ ጋር የሚጣጣም ሆኖ መሻሻል እንዳለበት ከላይ ጠቅሻለሁ።
የፌዴራል ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ሂደቱ ላይ ግን በኢትዮጵያውያን ባለ ድርሻ አካላት መካከል ስምምነት ያለ አይመስለኝም።
እያንዳንዱ ግለ ሰብ የየራሱ የሆነ አስተሳሰብ አለው። ይህንን ሃሳቡን ደግሞ በነጻ ለመግለጽ ያልተገደበ መብት አለው።
ስለዚህ ሕገ መንግሥቱን በተመለከተ የማይጣጣሙ አስተሳሰቦችን ማስተናገድ ፍጹም ተፈጥሮያዊ ነው። ተፈጥሮያዊ የማይሆነው ግን “የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው፣ ያንተ የተሳሳተ ነው፣ ስለዚህ የኔን ሃሳብ መቀበል አለብህ አለ በለዚያ ካንተ ጋር በእኩልነት የመወያየት ግዴታ የለብኝም፣ ከተቻለም አሸንፌህ የራሴን ሃሳብ ብቻ እንዲተገበር አደርጋለሁ” ማለቱ ላይ ነው።
ዛሬ በአገራችን እያስተናገድን ያለውን ቀውስ በተለይም በማንነት ጥያቄ ዙሪያ ያሉ አለ መግባባቶችንና ግጭቶችን ለመፍታት ከመፍትሔዎቹ አንዱ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ወይም መፋቅ መሆኑን ካመንንበት፣ ሙያተኛ ባለ ድርሻ አካላት የተለያዩ ሃሳቦቻችንን ነጻና ግልጽ በሆነ መንገድ ያለ አንዳች ተፅዕኖ የምንወያይበትና ሃሳብን በሃሳብ የምንሞግትባቸውን ዲሞክራሲያዊ መድረኮች መፍጠር አለብን ባይ ነኝ።
መድረኮቹ ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት መሆን ያለባቸው ሲሆን ሂደቱ ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው ድረስ አካታች መሆን አለበት። መድረኮች ያልኩት፣ እንዲቋቋም የማሳስበው አንድ መድረክ ሳይሆን፣ ኢትዮጵያውያን በያሉበት አካባቢ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን እንዲከፍቱ ነው።
ውይይቱ በአካል ብቻ ሳይሆን በዘመናዊ ቴክኖሎጂም ድጋፍ ሊሆን ይችላል። ዋናው ቁም ነገር ሃሳብን በሃሳብ በሠለጠነ መንገድ ሃሳብ አፍላቂዎችን ሳይሆን ሃሳባቸውን ብቻ የምንሞግትበት ግልጽና ነጻ የሆነ መድረክ መፍጠር ነው።
አዎ! ባዛሬው የአገራችን ሁኔታ አብዛኛው ምሑር በቀሰመበት ትምሕርትና ባካበተው ልምድ አገርን ለመርዳት ከመሞከር ይልቅ ባልተማረውና በማያውቀው የፖሊቲካ መስክ ተሠማርቶ የፖሊቲካ መድረኩን ማጣበብ ብቻ ሳይሆን እያቆሸሸ እንደ ሆነ ሁላችንም የምንረዳው ክስተት ነው።
ይህንን ደግሞ በሕግ ወይም በውግዘት ልናቆመው የማንችል እርግማን ስለ ሆነ፣ ሕገ መንግሥትን የማርቀቅ ሥራ፣ ከቀሰምኩት ትምሕርት ወይም ካካበትኩት ሙያ ጋር ይጣጣማል ብለን የምናምን ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ለጉዳዩ ቅድሚያ ሠጥተን መድረኩን ለመፍጠር ውይይት ብንጀምር ታሪካዊ ኃላፊነታችንንና ግዴታችን በአግባቡ የምንወጣው ይመስለኛል።
ፈጣሪ አስተውሎትን ያበርክትልን።
*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ ናቸው።
ስዊድን፣ ነሐሴ 2025 ዓ/ም
wakwoya2016@gmail.com