የተፈናቃዮችና የተመላሾች መብቶች እና የባለ ድርሻ አካላት ሚና (ለውይይት መነሻ)

ይህንን ጽሁፍ ለማቅረብ የገፋፉኝ ሁለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን ስደተኞችና ተፈናቃዮችን የሚመለከቱ ምክንያቶች ናቸው። የመጀመርያው ያገራችን ተፈናቃዮች መብት ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ፣ ሰሞኑን የአሜሪካው ፕሬዚዴንት ዶናልድ ትራምፕ፣ አገራቸው የታወቀችበትን የስደተኞችን ተቀብሎ የማስፈር ፕሮግራም በመቀየር ከዚህ በፊት በያመቱ ቢያንስ ቢያንስ ወደ 12,5000 የሚጠጉ ስደተኞችን ተቀብሎ የማስፈሩን ዓመታዊ ፕሮግራም ወደ 7,500 ዝቅ ማድረጋቸው ነው።

gettyimages-2210967189-612x612.jpg

65-year-old Genet Araya sits on her bed at Mekele Internally Displaced Person (IDP) centre, where she has been living since 17 October 2022. Credit: SOPA Images/SOPA Images/LightRocket via Gett

የአሜሪካ መንግሥት ከተመድ ጋር በመተባበር አገሪቷ በያመቱ ከመላው ዓለም የምታስተናግደውን አጠቃላይ ዓመታዊ የስደተኞች የሠፈራ ፕሮግራም (Refugee Resettlement) ከመቀነስ ባሻገርም መስተንግዶውን የለገሱት ለነጭ የደቡብ አፍሪካ ዜጎች መሆኑ ሌላው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኗል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ እነዚህን የደቡብ አፍሪካ ዜጎችን ወደ አሜሪካ ለማስፈር፣ ግለሰቦቹ በዓለም ዓቀፍ ሕግ በተደነገገው መሠረት የደቡብ አፍሪካን ድንበር አቋርጠው በሌላ አገር ጥገኝነት መጠየቅ ሳይኖርባቸው፣ ወደ አሜሪካ የሚወሰዱት ከገዛ አገራቸው መሆኑ እስከ ዛሬ ድረስ ያልተለመደ ልዩ አሠራር መሆኑ፣ የ1951 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጄኔቫ የስደተኞች ኮንቬንሽን ይዘት ከግንዱ መቦርቦር መጀመሩን ያመለክታል።

አሜሪካና፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ150 በላይ አገራት በፈረሙት የጄኔቫ ኮንቬንሽኑና ተጓዳኝ ፕሮቶኮል መሠረት አንድ ሰው ስደተኛ ለመባል፣ ኮንቬንሽኑ ውስጥ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ቢያንስ ቢያንስ የአንደኛውን መሥፈርት ሲያሟላና አስተማማኝ አካላዊና ሕጋዊ ጥበቃና ደኅንነት ለማግኘት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ያገሩን ድንበር አቋርጦ ወደ ጎረቤት አገር ወይም ራቅ ብሎ በመሄድ የፖሊቲካ ጥገኝነት መጠየቅ አለበት።

በተለምዶ፣ አሜሪካና ሌሎች የሠፈራ አገራት (Resettlement Countries) ከተመድ ጋር በመተባበር ከጥገኝነት አገራት (Asylum Countries) አስቀድመው ባስቀመጧቸው ብሔራዊ መሥፈርት መሠረት ያስፈልጉናል የሚሏቸውን ግለ ሰቦች ከስደተኞቹ መካከል መርጠው በየዓመቱ ወደ የአገራቸው አምጥተው ያሰፍሯቸዋል።

ምናልባት ከትራምፕ በኋላ የሚመጣው የአሜሪካ ፕሬዚዴንት መሻሻል ያደርግበት እንደሁ እንጂ፣ ካሁን ጀምሮ አሜሪካ ከመላው ዓለም በያመቱ የምታሠፍራቸው ስደተኞች ቁጥር 7,500 ብቻ ይሆናል ማለት ነው።

እንደ መካነ ኢየሩሳሌም የብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን አይቀሬ አገር በመሆን በሯን ክፍት አድርጋ ለዘመናት ስደተኞችን ተቀብላ በማስፈር የምትታወቀዋ አሜሪካ ዛሬ ላይ በሯን በትልቅ መቀርቀርያ መዝጋቷንና ትንሽ ገርበብ ብሎ የተከፈተውም ደግሞ ለነጮች ብቻ መሆኑን ኢትዮጵያውያን ልዩ ትኩረት እንዲሠጡት ያስፈልጋል።

የተፈናቃዮች መብት

ከላይ እንዳልኩት፣ ለዚህ ጽሁፍ ሃሳብ ዋናው ምክንያቴ የኢትዮጵያ ተፈናቃዮች ወቅታዊ ሁኔታ ነው።

ከዓለም ዓቀፍ ሕግ አንጻር ሲታይ በስደተኞችና በተፈናቃዮች መካከል ያለው ዋናውና ምናልባትም ብቸኛው ልዩነት፣ ስደተኛ ለመባል ብሔራዊ ድንበርን አቋርጦ ለሌላ አገር መንግሥት እጅ መስጠት ዋነኛው መሥፈርት ሲሆን፣ ተፈናቃዮች ግን በተለምዶ ይኖሩበት ከነበረው ሠፈርና ቄዬ ልክ እንደ ስደተኞች ያለ ፈቃዳቸው ቢፈናቀሉም፣ ያገራቸውን ድንበር ስላላቋረጡ ብቻ ተፈናቃይ ይባላሉ።

ያፈናቀላቸውም ምክንያት ስደተኞቹን ካፈናቀላቸው ጋር አንድ ዓይነት ሊሆን ቢችልም፣ ብሔራው ድንበር ስላልተሻገሩ ብቻ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብታቸውን የመጠበቅና የማስጠበቅ ግዴታ ያለበት ብሔራዊው መንግሥት ወይም ብሔራዊ ታጣቂ ኃይላት ናቸው።

ዘላቂ መፍትሔ ፍለጋውና ቁሳቁሳዊ ዕርዳታ ለማድረግ ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ በመንግሥት ፈቃድ ጣልቃ ይገባ እንደሁ እንጂ፣ የዜጎቹን መብት የመጠበቅና የማስጠበቅ ኃላፊነቱ የመንግሥትና በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ መንግሥትን የሚፋለሙ የብሔራዊ ታጣቂ ኃይላት ነው።

ሕዝቦችን ከሚያፈናቅሏቸው ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ፣

ሰላማዊ ሕዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች ከቄያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ሰው ሰራሽ ሲሆኑ የዚያኑ ያሕል ደግሞ ተፈጥሮያዊ ምክንያቶች አሉ። ጥቂቶቹን ብቻ ለመጥቀስ ያህል፣

ሀ) ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ፣ ለምሳሌም የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ መንግሥት የሕዝቦችን ሰብዓዊና ሕገ መንግሥታዊ መብቶችን ሲጥስ፣ ለማስከበር ሳይችል ወይም ሳይፈልግ ሲቀር፣ በጽንፈኞች ውትወታና በተለያዩ ምክንያቶች በሕዝቦች መካከል በሚከሰት የጎንዮሽ (የእርስ በርስ) ግጭቶች ምክንያት፣

ለ) ከሰው ልጆች ቁጥጥር በላይ የሆኑ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ምክንያት (ጎርፍ፣ መሬት መንቀጥቀጥ፣ እሳት አደጋ፣ ድርቅ፣ ወዘተ፣) የሚሉ ናቸው።

አብዛኞቹ የታዳጊ አገር ተፈናቃዮች በአጠቃላይ እና ያገራችን ተፈናቃዮች ደግሞ በተለየ መልኩ፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አርሶ ወይም አርብቶ አደር ሲሆኑ፣ አልፎ አልፎ የጥቃቅን ጎጆ እንዱስትሪ ባለቤቶችና ነጋዴዎችም ይገኙባቸዋል።

በመሆኑም፣ ተፈናቃዮቹ ከቄዬያቸው ማለትም፣ ከእርሻና የግጦሽ መሬት ወይም ከውሃ ምንጮች ጋር ያላቸው ቁርኝት በጣም ጥብቅ ነው። ያላቸው ዋነኛ ምድራዊ የማይንቀሳቀስ ንብረታቸው የሚያርሱት መሬትና ከብቶቻቸውን የሚያረቡበት ሜዳ ስለሆነ ከተፈናቀሉ በኋላ ወደ ቄዬያቸው/መሬታቸው የመመለስ ፍላጎታቸው እጅግ በጣም ከፍተኛ ስለሆነ ከቄዬያቸው እምብዛው ርቀው አይሰፍሩም። በተለይም ደግሞ፣ ቄያቸውና መሬታቸው በአፈናቃዩ ኃይል ተወስዶባቸው ወይም ሊወሰድ ታቅዶ ከሆነ!

የኢትዮጵያ ተፈናቃዮች

አዲስ አበባ የሚገኘው የተመድ ስደተኞች ኮሚሽን በሰኔ 2025 ዓ/ም ባወጣው ኦፊሴላዊ ዘገባ መሠረት፣ በአገራችን ዛሬ 1.9 ሚሊዮን ተፈናቃዮች ይገኛሉ። ዘገባውን ዘርዘር አድርገን ስናየው ደግሞ ተፈናቃዮቹ 749,534 ኦሮሚያ ክልል ውስጥ፣ 749,509 ትግራይ ክልል ውስጥ፣ 166,353 ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ ሲሆኑ፣ 123,767 ደግሞ አፋር ክልል ውስጥ ተፈናቅለው መኖራቸውን ያመለክታል።

የአገራችን የፖሊቲካና ማኅበረሰባዊ ቀውሱ ሁሉ እንዳለ ሆኖ፣ ፖሊቲከኞች፣ ምሑራንና አክቲቪስቶች ስለ እነዚህ ሁለት ሚሊዮን ተፈናቃዮች ወቅታዊ ሁኔታ ወይም መብት ያላቸው ግንዛቤ በጣም የተለያየ ነው።

ትኩረታቸው አብዛኛውን ጊዜ በተጣሰው የተፈናቃዮቹ መብትና ዘላቂ መፍትሔ ፍለጋ ላይ ሳይሆን፣ የተፈናቃዮቹን ደካማ ጎን በመጠቀም፣ የራሳቸውን የፖሊቲካ ሥልጣን ዓላማ ማሳካቱ ላይ ስለሆነ፣ ለተፈናቃዮቹ ዘላቂ መፍትሔ የማግኘቱን ጉዳይ እጅግ በጣም ያወሳስቡታል።

በተመድና በዓለም ዓቀፉ ማኅበረ ሰብ የአሠራር ልምድ መሠረት ተፈናቃዮችን በተቻለ መጠን ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው በአፋጣኝ ወደ ቄዬያቸው እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ፣ ፖሊቲከኞቹና አክቲቪስቶቹ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቃዮቹ ወደ ቄያቸው እንዳይመለሱ ዕንቅፋት እየሆኑ ነው።

የዚህ ተቃራኒ ደግሞ አንዳንድ ፖሊቲከኞች ወይም አክቲቪስቶች፣ ተፈናቃዮቹ ያለ አንዳች መዘግየት ወይም ቅድመ ሁኔታ ዛሬውኑ ወደ የሰፈራቸው መመለስ አለባቸው የሚለው ነው። ይህም በጣም አደገኛ አካሄድ ነው።

የማፈናቀሉ መንሥዔ/ምክንያት በውል ታውቆ መፍትሔ ተገኝቶለት ሙሉ በሙሉ ሳይወገድ፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቄዬያቸው መመለስ በሕይወታቸው ላይ ቁማር እንደ መጫወት ነው።

የተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው መመለስ በምንም መልኩ ወይም ለምንም ዓላማ ለድርድር መቅረብ የሌለበት ጉዳይ ነው። ድርድር ካስፈለገ ደግሞ፣ በአፈናቃዮችና በተፈናቃዮቹ መካከል ሰላም ወርዶ፣ የመፈናቀሉ መሠረታዊ ምክንያት ተወግዶና፣ መወገዱን ደግሞ ሁለቱም ወገኖች አምነውበት፣ እንደ ድሮያቸው በመልካም ጉርብትናና ወዳጅነት አብረው በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ መንገድ የሚከፍት እንጂ መመለስን የሚያደናቅፍ ድርጊት መሆን የለበትም።

ተፈናቃዮች በቶሎ ወደ ቄያቸው መመለስ አስፈላጊ የሆነበትን ብዙ ምክንያት ማንሳት ይቻላል። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያሕል፣ የመፈናቀል ምክንያቱ ዘር ተኮር (ማንነት) ከሆነ፣ አፈናቃዩ ወገን የማይፈልጋቸውን ሕዝቦች በጉልበት አፈናቅሎ፣ መሬቱን ለራሱ ብሔር ተወላጅ ብቻ ስለሚያደርግ፣ የዘር/ጎሳ/ብሔር ኤንጄንሪንግ (ethnic engineering) ያስከትላል።

የብዙ ሕዝቦች መኖርያ የነበረው ሠፈር ወይም መንደር/ግዛት የአንድ ብሔር/ሕዝብ ብቻ “ንጹሕ ግዛት” ይሆናል ማለት ነው። ተፈናቃዮቹ ከቤታቸው ርቀው የመኖራቸው ጊዜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ደግሞ፣ ወጣት ተፈናቃዮቹ አዲሱን ሰፈር እየለመዱ (አዲስ ትምሕርት ቤት፣ አዳዲስ ጓደኞች፣ ወዘተ) የትውልድ ሰፈራቸውን ቀስ በቀስ እየረሱ ይሄዱና ለመመለስ ያላቸው ፍላጎት እየመነመነ ይሄዳል።

አዛውንቶቹ ደግሞ በተፈጥሮ ሂደት ምክንያት ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው ለመመለስ አቅም ያጥራቸዋል። በነዚህና በሌሎች ተመሳሳይ ምክንያቶች ነው ተመድና የዓለም ዓቀፉ ማሕበረ ሰብ፣ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸው፣ ተፈናቃዮቹ በቶሎ ወደ ቄያቸው መመለስ አለባቸው ብለው የሚወተውቱት!

መደምደምያ

በቦታው ሆኖ ትክክለኛ መረጃ መሰብሰብ ባይቻልም፣ አብዛኞቻችን፣ ከሩቅ ሆነን ከምናገኛቸው መረጃዎች ብቻ ተነስተን ብንገመግም፣ ከወልቃይት የተፈናቀሉት የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ጉዳይ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ በጣም የተወሳሰበ ሆኖ እናገኘዋለን።

በኔ ግምት፣ የወልቃይት ፖሊቲካዊና አስተዳደራዊ ዕውነታ (ወልቃይት የማን ናት? በየትኛው ክልል ሥር መተዳደር አለባት ወዘተ) ጉዳዩን በጣም ያወሳሰበው ይመስለኛል።

ተፈናቃዮቹ ወደ ቀድሞ ቤታቸው በቶሎ እንዲመለሱ ከተፈለገ ግን፣ ተጻራሪ አስተሳሰቦችን ጥልቅና ቅንነት በተሞላበት ሁለንተናዊ ውይይት/ድርድር/ስምምነት መፍታት ግድ ይላል።

ያ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን፣ የወልቃይት ተፈናቃዮች ከየትኛውም ብሔር ይሁኑ፣ ወደ የትኛውም ክልል ይሰደዱ፣ ወደ ቀድሞ ቤታቸው ወደ ወልቃይት የመመለስ መብታቸው በምንም መልኩ ለድርድር የማይቀርብ ፍጹማዊ መብት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

ወደ ቀድሞ ሰፈራቸው መመለስ ለተፈናቃዮች መብት ሲሆን፣ ለመንግሥትና ለታጣቂ ኃይላት ደግሞ ግዴታ ነው።

ይህ ማለት ግን፣ የተፈናቃዮች የመመለስ መብት ገደብ የለሽ ነው ወይም የመንግሥት ግዴታ ደግሞ በአንዳችም ቅድመ ሁኔታ አይወሰንም ማለት አይደለም። ተፈናቃዮች፣ ሁኔታዎች ሳይመቻቹና ተመልሰው በሰላም ለመኖራቸው ዘላቂነት ያለው ዋስትና ሳይኖር ዝም ብሎ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መመለስ አለብን የሚል ገደብ የለሽ መብት የላቸውም።

መንግሥትም ደግሞ ሁኔታዎች ሳይመቻቹ ተፈናቃዮቹን አስገደዶ የመመለስ መብት የሌለውን ያህል፣ ሁኔታዎች ተመቻችተው እያለ ግን፣ ተፈናቃዮቹን ያለ በቂ ምክንያት ከመመለስ ሊገታቸው አይችልም። እንግዲህ ስለ ተፈናቃዮች የመመለስን ሁኔታ በተመለከተ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ላይ ስንሰብክ እነዚህን ተጓዳኝ ክስተቶችን ግምት ውስጥ መክተት አለብን ማለት ነው።

አሳዛኙ የአገራችን ፖሊቲካ አይሉት ባሕል፣ አንድ ኋላ ቀር የፊውዳል አስተሳሰብ ቢኖር፣ ለሰው ልጆች ይልቅ ለግዑዝ መሬት የምንሰጠው ክብር ነው።

ለምሳሌ በየሚዲያው ደጋግመን እንደምንሰማው፣ ብዙዎቻችንን የሚያሳስበው የወልቃይት ማንነት ወይም በየትኛው ክልል ሥር መተዳደር አለባት የሚለው እንጂ፣ ስለ ወልቃይት ተፈናቃዮች/ሕዝቦች ጉዳይ አይደለም። ይህ በጣም አሳዛኝ ነው።

ወልቃይት በአማራ ክልል ሥር ሆነች ወይም ወደ ትግራይ ክልል ተጠቃለለች እንደ መሬት አንዳችም የምትጎዳበት ነገር አይኖርም። ወልቃይት የትም ትሁን የት ያው ግዑዝ ምድር ናት። ስለዚህ ቅድሚያ መሠጠት ያለበት የወልቃይት ሕዝቦች ሕገ መንግሥታዊና ሰብዓዊ መብት መከበር እንጂ ወልቃይት በየትኛው ክልል ውስጥ ናት የሚል መሆን የለበትም።

ወልቃይትን ወልቃይት የሚያሰኛት ምድሪቷ ሳትሆን ወልቃይቴዎች ናቸውና!

በተረፈ ግን፣ በዛሬው የኢትዮጵያ ሁኔታ ግጭቶች ብሎም መፈናቅሎች በሚከሰቱባቸው አካባቢዎች ተገኝቶ እውነተኛ መረጃና ማስረጃ ሊያጋራን የሚችል ወገንተኛ ያልሆነ አንድም ግለሰብ ወይም የመንግሥት ጋዜጠኛ ወይም ታዛቢ ስለሌለ፣ እንደው ዝም ብሎ “በዚህ ቦታ በዚህ ሕዝብ ላይ ጄኖሳይድ እየተፈጸመ ነው” “ይኸኛው ሕዝብ ያኛውን ሕዝብ እያረደ ነው” ወዘተ እያልን፣ በሌላ አገር የተፈጸመን ጥቃት በአገራችን እንደተፈጸመ አስመስሎ የውሸት ቪዲዮ እያሠራጨን፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻንና ቂም በቀልን ከመዝራት፣ የመፈናቀሉን መንሥዔ በበቂ አጥንተን ሕዝቦች በሰላም አብረው በዘላቂነት እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን መፍትሄ ፍለጋ ላይ ብናተኩር ለሁሉም ይበጃል ባይ ነኝ።

ሲሆን ሲሆን፣ ገለልተኛ አካላት ወይም የሚዲያ ተቋማት በቦታው ተገኝተው ወገንተኛ ያልሆነ ዘገባ እንዲያቀርቡልን እና በዘገባው መሠረት በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመሠረት ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ላይ ጫና ብናሳድር የተሻለ ይሆን ነበር።

ያለፈው አልፏል፣ አሁንም፣ ሰከን ብለን፣ እኛ “የተማርነው”፣ የየብሔሩ ጽንፈኞች በቀደዱልን ትክክል ያልሆነ የትርክት ቦይ እየፈሰስን ሕዝባችንን ለመፈነቃቀሉ እንደ ዳረግናቸው ተገንዝበንና፣ የኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ደግሞ እንደ ሕዝብ አንድም ጊዜ በእርስ በርስ ላይ ተነስቶ እንዳልተቆሳሰለ ግምት ውስጥ በመክተት፣ ግጭትን ከማባባስ ብንቆጠብና አብሮነትን በሚያለመልሙ እንቅስቃሴዎች ላይ ብንረባረብ የተሻለ ነው እላለሁ።

እስቲ ከፖሊቲካ ውጪ፣ የኢትዮጵያ ተፈናቃዮች በሰላም ወደ ቀድሞ ቤታቸው ተመልሰው ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖሩ መደረግ አለባቸው ብላችሁ የምታምኑበትን በሃሳብ ደረጃ አምጡና እንወያይበት።

*****

ስዊድን፣ ሚያዚያ 2025 ዓ/ም

*** ባይሳ ዋቅ-ወያ ቀደም ሲል በራሺያ ፌዴሬሽን - ሞስኮ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ ሆነው ያገለገሉ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለ ናቸው።
wakwoya2016@gmail.com


Share

8 min read

Published

By Bayisa Wak-Woya

Source: SBS



Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service