በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ የኢትዮጵያ ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር የኢትዮጵያውያን ማኅበርሰብ አባላትን ዛሬ እሑድ ኦክቶበር 3 ማምሻ ላይ በበይነ መረብ ተሰናበቱ።
ዘመኑ ያፈራውን የዘመነ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ ያሉ ሚሲዮኖቹን አሠራርና አመዳደብ አጠናክሮ መጠቀም እንደ አማራጭ በመወሰዱ የአውስትራሊያና ኒውዝላንድ አምባሳደር ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ሆኖ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ሌሎች የቆንስላ ግልጋሎቶች አሰጣጥ የማሻሻያ ለውጥ ሥራ እየተካሔደ ስለሆነ ሲጠናቀቅ እንደሚገለጥ፣ የቪዛ አገልግሎቶች በኦንላይን መጠቀም እንደሚቻልና ሌሎች አገልግሎቶች ቶኪዮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደሚከናወን አስረድተዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ጉዳያቸው የተስተጓጎለባቸውን ሰዎች ይቅርታ ጠይቀዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም፤ የዳያስፖራውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ የኢትዮጵያውያን ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚቀጥል አመላክተው፤ የማኅበረሰቡ አባላት "በተናጠልም ሆነ በጋራ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆናችሁ እንድትቀጥሉ አደራ እላለሁ" ብለዋል።
አክለውም፤ በአውስትራሊያና ኒውዝላንድ ያሉ ኢትዮጵያውያን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ወቅት፣ ጦርነት በተቀሰቀሰበት፣ ለተፈናቃዮች በመለገስ፣ የሐሰት ትርክቶችን በመመከትና የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ስለ ኢትዮጵያ ሁሉንም ሆናችሁ ስላበረከታችሁት አስተዋፅዖ በመንግሥት፣ በኤምባሲውና በራሴ ስም አመሰግናለሁ" ብለዋል።
አምባሳደር ሙክታር በማያያዝ የማኅበረሰቡ አባላት ይህንኑ ተግባራቸውን እንደሚቀጥሉ ያላቸውን ተስፋ ጠቅሰው፤ "በየደረስኩበት የእናንተን አገር ወዳድነትና ስለ በጎነታችሁ
እናገራለሁ። በአካል እንጂ በመንፈስ አንድ ነን። እዚህ የነበረኝ ቆይታ አጭር ቢሆንም ቆይታችንን ፍሬያማና የማይረሳ ስላደረጋችሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ። ነገ ከሚመሰረተው መንግሥት ጋር ኢትዮጵያ ዳግም ፈክታና ደምቃ እንድንገናኝ እመኛለሁ" በማለት ተሰናብተዋል።
በስንብቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ታዳሚ የነበሩ የማኅበረሰብ አባላት የተለያዩ የምስጋና፣ ማሳሰቢያና የፖሊሲ አቅጣጫ ማመላከቻ ዕሳቤዎችን ለተሰናባች ዲፕሎማቶች አቅርበዋል።
በማጠቃለያም በካንብራ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማት ግዛቸው አዲስ በበኩላቸው "ይህን ዕድል ለሰጠችኝ አገሬና መንግሥቴ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። ግንኙነታችን የነበረው በአገልጋይነትና ተገልጋይነት ሳይሆን ቤተሰባዊነትን የተላበሰ ነበር። አመሰግናለሁ" ብለዋል።

Diplomat Gizachew Addis. Source: SBS Amharic
ከማኅበረሰቡ አባላት የቀረበ የስንብት ስጦታም ለአምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ተበርክቷል።