ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ 12 በአገር ውስጥና በውጭ አገራት ለሚገኙ መላው ኢትዮጵያን የአንድ ሺህ 442ኛው ዓመተ ሒጅራ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዒድ አል-አድሐ ዐረፋ በዓልን ታላቅነትና የመስዕዋት በዓል መሆኑን ነቅሰው "የዘንድሮውን የዐረፋ በዓል የምናከብረው እንደ ሀገር በሁለት አቅጣጫዎች እየተፈተንን ነው። በአንድ በኩል በሕዳሴ ግድባችን ዙሪያ የዘመናት ምኞታችን እውን እንዲሆን፣ የዓመታት ልፋታችን ፍሬ እንዲያፈራ የመጨረሻውን ተጋድሎ በማድረግ ላይ እንገኛለን። በሌላ በኩል አንድነታችንን ከሚሸረሽሩና ሀገራችንን ከጀርባ እየወጓት ከሚገኙ እኩይ ኃይሎች ጋር እየተፋለምን ነው። አሁን ለሀገራችን ያለንን ጥልቅ ፍቅር በተግባር የምናሳይበት ወሳኝ ወቅት ነው። በሀገር ጉዳይ እስከ ምን ድረስ ለመፈተን ዝግጁዎች መሆናችንን ልናስመሰክር ይገባል" ብለዋል።
የኢትዮጵያን በዲፕሎማሲው ዘርፍ መፈተንና የሕዳሴ ግድብን ሙሌትን ሲያመላክቱም "የሚገጥሙንን የዲፕሎማሲና ሁለንተናዊ ጫናዎች ተቋቁመን በጽናት እንጓዛለን። እስከ አሁን አንደኛውና ሁለተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት በድል ማጠናቀቅ ችለናል። በዚህ መልኩ እውነትን ይዘን በትብብርና በመናበብ መጓዛችንን ከቀጠልን ያለጥርጥር ፍጻሜአችን ያምራል" በማለት አበረታተዋል።
አያይዘውም አገር ቤትና ባሕር ማዶ ላሉ ኢትዮጵያውያን ምሥጋናቸውንና ዘላቂ ተስፋቸው ሲገልጡ "በዚህ አጋጣሚ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሆናችሁ በሕዳሴ ዙሪያ ስትፋለሙ ለነበራችሁ ሁሉ ያለኝን አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ። ሀገር ፍቅራችሁን በምትሻበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ከጎኗ በመቆማችሁ፣ አስፈሪ የሚመስሉ ተገዳዳሪዎቿን በድፍረት በመጋፈጣችሁ፣ በኢትዮጵያ ስም ሳላመሰግናችሁ አላልፍም። ወደፊትም አይተኬ ሚናችሁን አጠንክራችሁ እንደምትገፉበት ተስፋ አለኝ" ብለዋል።
አክለውም "የዛሬውን የመስዕዋት በዓል ከሙስሊም ወገኖቻችን ጋር ሆነን በምናከብርበት በዚህ እለት፣ ሀገራችንን አደጋ ላይ እየጣላት የሚገኘውን የጁንታ ሐይል ለመፋለም በዱር በገደሉ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኙ ወገኖቻችን አሉ። ዐረፋን ስናከብር እነዚያን መስዕዋት የሚሆኑ ወንድሞቻችንን እያሰብንና ተገቢውን ክብር እየሰጠናቸው መሆን አለበት" በማለት አሳስበዋል።
የበዓሉን ማኅበረሰባዊ ዕሴቶችንም በማንሳት "በዓሉ በዓል የሚሆነው ሙኢምኑ ተረዳድቶና አንድ ሆኖ ሲያከብረው ነው። መረዳዳትና መተሳሰብ ሀገርን ከፈተና የሚያወጣና ወደምትፈልገው ደረጃ የሚያደርስ ዕሴት ነው። ኢትዮጵያውያን ያለንን ሁሉ አውጥተን፣ የተማሩ ላልተማሩ፣ ያላቸው ለሌላቸው፣ የሚችሉ ለማይችሉ፣ የተረዱ ላልተረዱ አካፍለው ይሄን ያለንበትን ፈታኝ ጊዜ ማለፍ እንዳለብን አረፋ ያስተምረናል" ሲሉ አስገንዝበዋል።
መልዕክታቸውንም ሲቋጩ "በድጋሚ መልካም የዐረፋ በዓል እንዲሆንላችሁ እየተመኘሁ፣ በእለቱ ድኾችን፣ በየመጠለያው ያሉ ወገኖችን፣ በየሕክምና ማዕከሉ ያሉትን ሕሙማን እንድናስባቸው አደራ እላለሁ፡፡ ዒድ ሙባረክ!!" ብለዋል።